Fana: At a Speed of Life!

በመዲናዋ ሀሰተኛ ሰነዶችና ማስረጃዎችን ሲያዘጋጁ የነበሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 20፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአዲስ አበባ ሀሰተኛ ሰነዶችንና ማስረጃዎችን ሲያዘጋጁ የነበሩ 13 ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ገለፀ።

በቁጥጥር ስር ከዋሉት ግለሰቦች መካከል ሰባቱ በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት የወሳኝ ኩነት ሰራተኞች ሲሆኑ÷ ስድስቱ ደግሞ በንፋስ ስልክ ክፍለ ከተማ በመኖሪያ ቤታቸው ሕገወጥ ማስረጃዎቹን ሲያዘጋጁ በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች ናቸው፡፡

የጸጥታ አካሉ ባደረገው ፍተሻም 81 የሚደርሱ የመንግስትና የግል ተቋማትን ተመሳስለው የተዘጋጁ ሐሰተኛ ክብና የራስጌ ማሕተሞች ተይዘዋል።

በአዲስ አበባ ፖሊስ የሙስና እና ገቢዎች ልዩ ልዩ ወንጀሎች ዳይሬክተር ኮማንደር ደሪቤ ገዳ ዛሬ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ÷ ግለሰቦቹ ሐሰተኛ ሰነዶችን ሲያዘጋጁ እጅ ከፍንጅ ተይዘው በቁጥጥር ውስጥ ውለዋል።

እነዚሁ አካላት በዋናነትም ህገ-ወጥ ሰነዶችን ለአሸባሪው ህወሃት ሰረጎ ገቦች በማዘጋጀት ሰላምና ደህንነትን ለማወክ ጥረት ሲያደርጉ እንደነበርም ጠቅሰዋል፡፡

በወንጀሉ ከተጠረጠሩት ውስጥ በአንድ ግለሰብ መኖሪያ ቤት 262 ሺህ 840 ብር በፍተሻ መያዙን ገልጸዋል።

ያላገባ የምስክር ወረቀት፣የቀበሌ መታወቂያ፣የሽያጭ ውል፣ ፓስፖርት፣ ላፕቶፕ፣ ቲተር፣የልደት ምስክር ወረቀት እና ሌሎችን ሰነዶች ከተያዙትት የሚጠቀሱ መሆኑን ኢዜአ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.