Fana: At a Speed of Life!

ከአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የተሰጠ መግለጫ

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ካለፉት አራት ዓመታት ጀምሮ የክልሉን ሕዝብ በኢትዮጵያ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ሥር ተጠቃሚ የሚሆንበትን ወሳኝ ተግባራት አከናውኗል። ይህን ሁኔታ የተረዳው አሸባሪው የሕወሐት ቡድን የአማራ ሕዝብና መንግሥት የራሱን የመልማት ዐቅም ተጠቅሞ የራሱን ዕድገት የሚያረጋግጥበትን ዕድል ለማጨናገፍ ከመነሻው ዓላማ ይዞ እንደሚንቀሳቀስ ይታወቃል።

በቀጥተኛ እና በተዘዋዋሪ መንገድ በመላ ኢትዮጵያ በሚገኘው የአማራ ሕዝብን ላይ የተጠኑ፤ ተከታታይነት ያላቸው፣ አሰቃቂ ዘር ተኮር ጥቃቶችን፤ ግድያዎችን፤ ዝርፊያና መፈናቀል እንዲደርስበት በማድረግ አማራን ማኅበራዊ ዕረፍት የመንሣት ስልትን ሲከተል ከርሟል፡፡
በዚህ የጥፋትና የእልቂት ድርጊቶቹ ያልተገታው ሽብርተኛው የሕወሐት ቡድን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት አደጋ ላይ የሚጥል ክህደት ፈጽሟል። በዚህም በሀገር መከላከያ ሠራዊት ሰሜን ዕዝ ላይ ወታደራዊ ጥቃት አድርሷል። ከዚህም አልፎ በመልከአ ምድራዊ አቀማመጡም ሆነ በባህላዊና ሃይማኖታዊ መስተጋብሮች የሺ ዓመታት የአብሮነት ታሪክ ባለው የአማራ ክልል ሕዝብ ላይ ወረራ በመፈጸም ከፍተኛ ሰብአዊ ጉዳቶችን አድርሷል። ከ288 ቢልዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው መሠረተ ልማቶችና ተቋማትንም አውድሟል፡፡

የክልሉ መንግሥት በአማራ ሕዝብ ላይ የህልውና አደጋ ጋርጠውበት የነበሩትን እነዚህን ሁሉ ግፎች ለመከላከል ጥረት ከማድረግ በዘለለ ወደለየለት መጠፋፋት እንዳይገባ ከፍተኛ ጥንቃቄ በማድረግ የተፈጠሩት ግጭቶች ሁሉ በሰላማዊ መንገድ የሚፈቱበትን አማራጮች በማስቀደም ከሁሉም በፊት፤ከምንም በላይ ለሰላም ቅድሚያ ሰጥቶ ቆይቷል፡፡

ይሁን እንጂ ሽብርተኛው የሕወሐት ቡድን ለሰላም የተከፈተውን በር የጥፋት መናፍስቶቹ ማሹለኪያ በማድረግ በሚፈጽማቸው የጦርነት ትንኮሳዎችና ወረራዎች ስላለፈው የጋራ ታሪካችን እና ስለ መጪው አንድነት፤ዕድገትና ተስፋችን ስንል ቅድሚያ የሰጠነውን የሰላም ዕድል በተደጋጋሚ አምክኗል፡፡

ዛሬም ቢሆን ለትግራይ ክልል አዋሳኝ በሆኑ የክልላችን አካባቢዎች ላይ ለአራተኛ ጊዜ ወረራ በመፈጸም ከወራት በፊት በክልላችን ሕዝብ ላይ የፈጸመውን ሁለንተናዊ ጥቃት ለመድገም እየተክለፈለፈ ይገኛል፡፡
ይህ ጦር ናፋቂ የሽብር ቡድን በንጹሐን ዜጎች፤በሃይማኖታዊ እና ዓለም አቀፋዊ የሰብአዊ ድጋፍ ሰጪ ተቋማት ላይ የፈጸማቸው ጥቃቶች የቡድኑን እውነተኛ ማንነት አጋልጠውታል። በመሆኑ መላው ሰላም ፈላጊ የሰው ዘር እና ዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ የሽብር ቡድኑን ሊያወግዝ እና ለፈጸመው ወንጀል ተጠያቂነት ሊያደርጉት ይገባል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ሁሉንም ዓይነት ግጭቶች በሰላማዊ መንገድ ብቻ እንዲፈቱ የሰነቀው ልባዊ መሻት ጽኑ ነው። ነገር ግን በአሸባሪው የሕወሐት ቡድን እምቢተኝነት ምክንያት የሰላም አማራጮች የተዘጉ በመሆናቸው የክልሉ መንግሥት የሕዝቡን ደኅንነት የማስጠበቅ መንግሥታዊ ግዴታውን እንዲወጣ አስገድዶታል።

ስለዚህም በአሸባሪው የሕወሐት ቡድን የተቃጣበትን ወረራ ለመቀልበስ የሚያስችል አስፈላጊና ተመጣጣኝ ዝግጅት በማድረግ ላይ ይገኛል፡፡
በመሆኑም መላው የአማራ ሕዝብ የክልሉ መንግሥት የሚያቀርበውን ጥሪ በንቃት እንዲጠብቅና ተገቢውን ሁሉ ዝግጅት እንዲያደርግ የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከወዲሁ ያሳስባል፡፡

የአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት
ነሐሴ- 21/2014ዓ/ም
ባሕር ዳር

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.