Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ በተባበረ ክንዳችን እንቀለብሳለን – የደቡብ ክልል

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ በተባበረ ክንዳችን እንቀለብሳለን ሲል የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡

የክልሉ መንግስት በወቅታዊ ሀገራዊ ሁኔታ ላይ ባወጣው መግለጫ÷ ከሰላም ይልቅ ጦርነትን መርጦ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመዳፈር አልሞ እየተንቀሳቀሰ የሚገኘውን  የህወሓት ሽብር ቡድን ለመደምሰስ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል ዝግጁ  መሆኑን አረጋግጧል፡፡

አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊ ማዕበል በመጠቀም የቃጣብንን ወረራ በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግም በመግለጫው ተመላክቷል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

አሸባሪው ህወሓት በአማራ እና አፋር ክልሎች የጀመረውን ወረራ በተባበረ ክንድ ለመቀልበስ የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት  ዝግጁ ነው።

ከሰላም ይልቅ ጦርነትን መርጦ የሀገርን ሉዓላዊነት ለመዳፈር አልሞ እየተንቀሳቀሰ ያለውን የሽብር ቡድን እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ አስፈላጊውን መስዋዕትነት ለመክፈል የክልሉ መንግስት ዝግጁ ነው።

መላው የክልላችን ህዝቦች ሀገር በጠላት በተወረረች ጊዜ የህይወት መስዋዕትነት እየከፈሉ ላሉ ጀግኖቻችን በስንቅ ዝግጅት፣በሞራል፣ከዚህ ባለፈም ወደ ግንባር በመዝመት አለኝታቸውን አሳይተዋል።

ሰርተን መለወጥ የምንችለው ሀገር ሰላም ስትሆን እንደመሆኑ መጠን አሸባሪው ህወሀት ህዝባዊ ማዕበል በመጠቀም የቃጣብንን ወረራ በአስተማማኝ ደረጃ ለመመከት የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ የሚያደርግ ይሆናል።

አሸባሪው ህወሓት በስልጣን ላይ በቆየባቸው ዓመታት በህዝብ ደም ሲነግድ ቆይቷል።እኔ ያልመራኋት ሀገር መፍረስ አለባት በሚል እሳቤ ለሰላም የተዘረጋውን አማራጭ ወደ ጎን በመተው ለጋ ህጻናትን በማሰለፍ ግልጽ ወረራ መጀመሩን መላው የአለም አቀፍ ማህበረሰብ ሊገነዘብ ይገባል።

የሽብር ቡድኑ በንጹሀን ዜጎቻችን ላይ ካደረሰው ጭፍጨፋ በተጓዳኝ ከውጭ ታሪካዊ ጠላቶቻችን ጋር በመተባበር ኢኮኖሚያችን እንዲዳከም ጥረት አድርጓል። ከዚህ ቀደም ተዋደው እና ተግባብተው በሚኖሩ ህዝቦች መካከል ግጭት እንዲኖር የዘወትር ተግባሩ አድርጎ ቆይቷል።በሌላ በኩል የብሔር እና የሀይማኖት ግጭት በመፍጠር ሀገሪቱን የትርምስ ቀጠና ሲያደርግ እንደነበርም ልብ ሊባል ይገባል።

አሸባሪው ህወሓት ተላላኪዎቹን በመጠቀም  የህብረ ብሔራዊነት ተምሳሌት የሆነውን ክልላችንን በማወክ ለብዙሀን ሞት፣መፈናቀል፣የንብረት ውድመት እና የአካል ጉዳት እንዲከሰት ምክንያት ሆኗል።

የሀገርን ዳር ድንበር እየጠበቀ ባለው በመከላከያ ሠራዊት የሰሜን እዝ ላይ ከፈጸመው ክህደት ጀምሮ የትግራይ ወጣቶችን ወደ ጦርነት በማስገባት በአማራና አፋር ክልሎች በፈጸመው ግልጽ ጦርነትና ወረራ ያደረሰው እልቂት አሸባሪ ቡድኑ ለሰብዓዊነት ምንም የማይራራ አረመኔ መሆኑን በግልጽ የሚያሳይ ነው።

መላው የሀገራችን ህዝብ ሀገር በጠላት ስትወረር ከዳር እስከ ዳር ሆ ብሎ በመነሳት ጠላትን አሳፍሮ መመለስ  ከጀግኖች አባቶቻችን የወረስነው አኩሪ ታሪክ አለን ይህም እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በአሁኑ ትውልድ የሚደገም ይሆናል ።

በአማራና አፋር ክልሎች የደረሰውን ወረራ የክልሉ መንግስት የሚያወግዝ ሲሆን መንግስት ተገዶ የገባበትን ህግ የማስከበር እርምጃ የምንደግፍ ይሆናል።

የደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት

ነሐሴ 22/2014 ዓ.ም

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.