Fana: At a Speed of Life!

መከላከያ ሠራዊት ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየፈፀመ መሆኑን አስታወቀ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 22፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት የሁሉም ኢትዮጵያዊ ጠባቂ በመሆኑ ሀገራዊና ህዝባዊ ኃላፊነቱን በከፍተኛ ጥንቃቄ እየፈፀመ እንደሚገኝ አስታወቀ፡፡
 
መከላከያ ሠራዊት በዛሬው ዕለት ባወጣው መግለጫ እንደገለጸው÷ አሸባሪው ህወሓት የትግራይን ወጣት እየማገደ በሕዝብ ማዕበል ማጥቃቱ፣ እኔ እየመራሁ የማልዘርፋት ሀገር ትፍረስ እኩይ ተግባሩና ፀረ ህዝብ ባህሪው አንፃር የሚጠበቅ ነው።
 
በተቃራኒው እኛ ግን የመላው 120 ሚሊየን በላይ ኢትዮጵውያን ደህንነት የመጠበቅ ኃላፊነት ተቀብለን የምንፈፅም ህዝባዊና ፕሮፌሽናል ብሔራዊ ኃይል ስለሆንን መላውን ህዝባችንና የትግራይን ጨቅላ ህፃናት ከከንቱ እልቂት የመታደግ ሞራላዊና ህጋዊ ግዴታ አለብን ነው ያለው፡፡
 
ህወሓት ያኔ ጥንት በአንደኛው የዓለም ጦርነት ስልጣኔና የዘመነ ጦር መሳሪያ ባልነበረበት ጊዜ ጦርነትን በሰው ማዕበል ገጥመህ ማሸነፍ ወረት በነረበት ወቅት እንደሚደረገው ከግብረ-ገብ፣ ከሞራልና ህጋዊነት በእጅጉ በተጣረሰ አኳኋን ገና በሰውነታቸው ያልጠነከሩ ጨቅላና ለጋ ህፃናት ከኋላ በሃይል እየገፋ በሚገባ ሰልጥኖ እስከ አፍንጫው ከታጠቀ የመከላከያና ጥምር ኃይል ፊት እያሰለፈ የእሳት እራት አድርጎ በማስፈጀት የሞት ቀኑን ለማዘግየት ታሪክ ይቅር የማይለውን ጭካኔ በገዛ ወገኑ፤ ወገናችን የትግራይ ህዝብ ላይ እየፈፀመ መሆኑንም ጠቁሟል፡፡
 
ስለዚህም ሰራዊታችን በህግ የተቋቋመ፣ በህግ የሚመራና በህዝብ በተመረጠ መንግስት የሚታዘዝ፤ ሲያለማ እደሚሞገስና እንደሚሸለም ሁሉ የተሰጠው ህገ-መንግስታዊ ተልዕኮ በሚገባ ሳይፈፅም ሲቀርና ሲያበላሽ በሀገሪቱና ዓለም አቀፍ ህጎች የሚጠየቅና የሚዳኝ ሀገራዊ ኃይል እመንደሆነም መግለጫው አውስቷል፡፡
 
ስለሆነም መከላከያ ሰራዊት ህግን ተከትሎ ወገኑን ከሰቆቃና እልቂት ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ መስዋዕትነት በጀግንነት በመክፈል የኢትዮጵያን የግዛት አንድነትና ብሔራዊ ጥቅም ያስከብራል ነው ያለው፡፡
 
የሽብር ቡድኑ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች ተከፋይ፤ ጉዳይ አስፈፃሚና በወንጀል የሚፈለግ ህገ-ወጥ ሽፍታ መሆኑን ያመላከተው ሰራዊቱ ÷ቡድኑ የኃላፊነትና የተጠያቂነት መንፈስ አይሰማውም፤ በባህሪው ምክንያት ሊሰማውም እንደማይችል አስረድተዋል፡፡
 
በዚህ ሳቢያም የሽብር ቡድኑ እንደፈለገው የሚዋሽ እና የግፎች ሁሉ ጥግ የሆነ ተግባር በገዛ ወገኑ ላይ የሚፈጽም መሆኑን አንስቷል፡፡
 
ስለሆነም መከላከያ ሰራዊት ህዝባችንን ከዚህ አሬመኔ ቡድን ቀንበር ለማላቀቅና ከከንቱ ጭፍጨፋ ለማዳን ህዝባችንና ለሀገራችን ይጠቅማል የተባለውን ሁሉ በመስዋዕትነታችን እውን ለማድረግ በከፍተኛ ብቃትና የላቀ የዝግጁነት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
 
ህዝባችን ከፍጅት ለመታደግ ሲባል መሆን የሚገባውን ሁሉ አጠቃላይ ሁኔታን በማያበላሽ አግባብ ቀጣይም ሊኖር እንደሚችል መታወቅ ይኖርበታልም ነው ያለው ፡፡
 
እኛ ታላቅና ታሪካዊ ኃላፊነት ካለበት የመከላከያ ኃይል በሚጠበቅ አግባብ፣ ሁለተናዊ በሆነና ነገን አሻግሮ በሚመለከት እሳቤ እንዲሁም በወታደራዊ ሳይንስና ጥበብ የምናደርገው እና እናንተ በጋለ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት ዛሬ፣ አሁን፣ እዚችው እዲሆን የምትፈልጉትን ሁሉ “አፍ በእጅ በሚያስይዝ” አስተማማኝና ዘላቂ በሆነ ድል ይታረቃል
ሲልም አረጋግጧል፡፡
ዛሬም ሆነ እስከ ወዲያኛው የኢትዮጵያን ክብርና ጥቅም ለመጉዳት የሚደረግ ከሰማይ በታች ያለ ፈተና ሁሉ እንደማንፈተን ታውቃላችሁ! ታምኑናላችሁም! ለኢትዮጵያ ብሔሮች፤ ብሔረሰቦች፤ ህዝቦች ደህንነት፣ የግዛት አንድነትና ለሀገረ መንግስቱ ቀጣይነት በመቆም የምንከፍለው መስዋእትነት ክብርና ኩራታችን ነው ብሏል መከላከያ ሰራዊት በመግለጫው፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.