Fana: At a Speed of Life!

ዓለም አቀፉ የሶላር አሊያንስ 4ኛ የአፍሪካ ቀጠና የኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 23፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዓለም አቀፉ የሶላር አሊያንስ አራተኛው ቀጠናዊ የኮሚቴ ስብሰባ በአዲስ አበባ ከተማ መካሄድ ጀምሯል፡፡
 
ስብሰባው የህብረቱ አባላት በአካል የተገናኙበት የመጀመሪያ መድረክ ሲሆን÷ የተዘጋጀውም ከኢትዮጵያ መንግሥት የውኃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤት ጋር በመተባበር መሆኑ ተገልጿል፡፡
 
በስብሰባው የህብረቱን ዋና ዳይሬክተር ዶክተር አጃይ ማቱርን ጨምሮ የኢትዮጵያ፣ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፐብሊክ፣ ጊኒ፣ ጋና፣ ማሊ፣ ጊኒ ቢሳው፣ ኮሞሮስ እና ሶማሊያ ሚኒስትሮች ተሳትፈዋል፡፡
 
ለ3 ቀናት በሚኖረው ቆይታ እስካሁን በነበሩት የሥራ ሂደቶች፣ ስኬቶች እና የወደፊት ዕቅዶች ላይ ይወያያል።
 
በተጨማሪም፥ የኅብረቱን የአምስት ዓመት ስትራቴጂክ ዕቅድ፣ በግሉ ሴክተር ስላለው ተሳትፎ፣ አቅምን ስለማጎልበት እና በፈረንጆቹ በ2030 ለማከናወን ለታቀደው የሶላር ኢንቨስትመንት ሥራ የተበጀተውን አንድ ትሪሊዮን ዶላር ጥቅም ላይ ማዋል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ እንደሚመክር ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.