በክልሉ ማዕድናትን በማልማት ለዜጎች የስራ ዕድል ሊፈጠር ይገባል – ም/ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 24፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የማዕድን አቅማችንን በማልማት ለዜጎቻችን ስራ ዕድል ልንፈጥር ይገባል ሲሉ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ ገለጹ ።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ውሃ፣ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ በማዕድንና ኢነርጂ ልማት ኤጀንሲ በማዕድን ልማት ስራዎች ዙሪያ ያተኮረ ምክክር መድረክ በተርጫ ከተማ እየተካሄደ ነው።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ነጋሽ ዋጌሾ ፥ “የማዕድን ዘርፉ ከልማት ስራዎች ቀድመን ከምንሰራባቸው መስኮች አንዱ ነው” ብለዋል፡፡
በዚህም በክልሉ ከፍተኛ የሆነ የማዕን አቅም ያለ በመሆኑ ይህንን በማልማት ለዜጎች የስራ ዕድል መፍጠር ይገባልም ነው ያሉት፡፡
ያሉትን ማዕድናት በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባ አንስተውም ፥ ዘርፉን በአግባቡ ለመምራት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት አስፈላጊ እንደሆነም አመላክተዋል።
በዘርፉ ለተሰማሩ ባለሃብቶችና ስራ ለሚፈጠርላቸው ዜጎች ምቹ ሁኔታ ለመፍጠር የተደራጀ የህግ ማዕቀፍ ማዘጋጀት አስፈላጊ እንደሆነም ነው ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ያነሱት።
የክልሉ ውሃ፣ማዕድንና ኢነርጂ ልማት ቢሮ ኃላፊ ኢንጂነር በየነ በላቸው የማዕድን ዘርፉ ያለበትን ማነቆ ለይቶ መንቀሳቀስ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በንቅናቄ መድረኩ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የዞን ዋና አስተዳዳሪዎች፣ የውሃ ማዕድንና ኢነርጂ መምሪያ ኃላፊዎች፣ በማዕድን ዘርፍ የተሰማሩ ባለሃብቶችና ባለድርሻ አካላት እየተሳተፉ መሆኑን ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!