ሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚሄደውን ዋና የጋዝ ማስተላለፊያ መሥመር ዘጋች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ሩሲያ በዋና የጋዝ ማስተላለፊያ መስመሯ ወደ አውሮፓ የምትልከውን የጋዝ አቅርቦት ለሦስት ቀናት ማቋረጧን አስታወቀች፡፡
እንደ ጋዝፕሮም መረጃ የጋዝ አቅርቦቱ የተቋረጠው “በኖርድ ስትሪም1” የጋዝ ማስተላለፊያ መሥመር ላይ ጥገና በማስፈለጉ ነው፡፡
ሩሲያ ወደ አውሮፓ የሚሄደውን የጋዝ አቅርቦት ያቋረጠችው ምዕራባውያን በጣሉባት ማዕቀብ ሀገራቱን ለመቅጣት በመፈለጓ ነው የሚለውን ውንጀላ ግን “ጋዝ ፕሮም” አጣጥሎታል፡፡
የጋዝ ማስተላለፊያ መሥመሩ ባሳለፍነው ሐምሌ ወርም እንዲሁ ለጥገና በሚል ለ10 ቀናት መዘጋቱ ይታወሳል፡፡
ከዚያ ወዲህ ከሙሉ ዐቅሙ 20 በመቶ ያኅሉን ብቻ በመጠቀም ለአውሮፓ ገበያ ጋዝ ሲያቀርብ እንደነበር አር ቲ ዘግቧል፡፡
የአውሮፓ ሀገራት መሪዎች ሩሲያ አሁን ላይ በ400 በመቶ የተወደደው የነዳጅ ዋጋ ይብሱኑ ለማናር የወሰደችው እርምጃ ነው በሚል ስጋታቸውን ገልጸዋል።
”ኖርድ ስትሪም 1” በሴንት ፒተርስበርግ አቅራቢያ ከሚገኘው የሩሲያ የባሕር ዳርቻ ተነስቶ በባልቲክ ባሕር ስር እስከ ሰሜን ምሥራቅ ጀርመን የሚዘልቅ የ 1 ሺህ 200 ኪሎ ሜትር የነዳጅ ማስተላለፊያ መሥመር ነው።
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!