አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት የትግራይ ወጣቶችን ወደ ሌላ እልቂት የሚመራ ነው – የትግራይ ተወላጆች
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት የትግራይ ወጣቶችን ለዳግም እልቂት የሚመራ ነው ሲሉ የትግራይ ክልል ተወላጆች ተናገሩ፡፡
ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉት የክልሉ ተወላጆች÷ ለትግራይ ቆሜያለሁ የሚለው ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ የትግራይን ህዝብ ለጦርነት እየማገደ ነው ሲሉ ኮንነዋል።
የክልሉ ተወላጅ አቶ ገብሩ በርሄ ÷ ህጻናት እና ወጣት የትግራይ ልጆች በትምህርት እና በስራ ማለፍ ያለበትን እድሜያቸውን፣ ህወሓሃት ለጦርነት እየማገደ ክልሉን ተተኪ አልባ እየደረገው ነው ሲሉ ወቅሰዋል።
ቡድኑ ከምዕራባውያንም ሆነ በውጭ እና በሀገር ውስጥ ካሉ የትግራይ ተወላጆች የሚያገኘውን ድጋፍ ለማስቆም እና የትግራይን ህዝብ ለመታደግ የክልሉ ተወላጅ ወጣቶች የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንድሚኖረውም ተናግረዋል።
አቶ ጊደና መድን በበኩላቸው÷ አሸባሪው ህወሓት እታገልላቸዋለሁ ካላቸው ዜጎች ጉሮሮ የእርዳታ እህል የመቀማት ልማድ እና የኋላ ታሪክ እንዳለው ጠቅሰው፥ ዛሬም እርዳታን የትግራይ ተተኪ ትውልዶች ነፍስ መለወጫ እያደረገው መሆኑን አንስተዋል።
ለትግራይ ቆመናል የሚሉት የቀድሞ ባለስልጣናት እና አሁንም ቡድኑን የሚደግፉት ግለሰቦች ዳግም የትግራይን ህዝብ ለጦርነት እየማገዱት መሆኑንም አመላክተዋል።
አሸባሪው ህወሓት እራሱን ለትግራይ ህዝብ የሚታገል አድርጎ ቢያቀርብም በተግባሩ ግን የትግራይ ህዝብ ጠላት መሆኑን አሳይቷል ነው ያሉት አቶ ጊደና መድን፡፡
የትግራይ ህዝብ እንደ ሌሎች ክልሎች ስለ ልማት መዘመር ሲኖርበት ተተኪ ትውልድን ለጦርነት እየማገደ ክልሉን ተስፋ አልባ እያደረገው መሆኑንም አንስተዋል።
ይህ አካሄዱ ስጋት ውስጥ እንደጣላቸው ያነሱት የክልሉ ተወላጆች፥ መላው የክልሉ ተወላጆችም የቡድኑን የጥፋት ጉዞ በቃ ሊሉ እንደሚገባም ጠይቀዋል።
በትዕግስት አብርሃም
ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!