Fana: At a Speed of Life!

አሸባሪው ህወሓት የሰላም አማራጮችን በመተው ወረራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ መሆኑን መንግስት ገለጸ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) መንግሥት ለሰላም አማራጭ ዕድል ለመስጠት ሲል የሕዝብ ማዕበል አስነሥቶ ሕጻናትን፣ ወጣቶችንና አረጋውያንን ለመማገድ የመጣውን የሕወሓት ታጣቂ በምሥራቅ አማራ በኩል በጀግንነት ሲከላከል መቆየቱን አስታውቋል።

ሕወሓት በምሥራቅ አማራ በኩል በቆቦና አካባቢው የከፈተው ወረራ በጀግናው የመከላከያ ሠራዊትና በደጀኑ ሕዝብ ጠንካራ የመከላከል ብቃት የተነሣ ባሰበው ልክ እንዳልሄደለትም አውስቷል።

በዚህም ምክንያት ለሰላም የተሰጠውን ሁለንተናዊ አማራጭ አሽቀንጥሮ ጥሎ ወረራውን ወደ ሌሎች አካባቢዎች እያስፋፋ ይገኛል ብሏል በወቅታዊ ጉዳይ ላይ የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ባወጣው መግለጫ።

ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው ሕወሓት፥ በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ መክፈቱንም ገልጿል።

ይህንን የሕወሓት ወረራ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ ይገኛልም ብሏል በመግለጫው።

የኢትዮጵያ መንግሥት በተለያዩ አቅጣጫዎች የተከፈቱበትን ጥቃቶች በጽናት እየተከላከለ አሁንም ለሰላም አማራጮች የዘረጋቸውን እጆች ዛሬም ድረስ አለማጠፉንም ነው ያስታወቀው።

ለሰላም የተዘረጋው እጅ በሕወሓት ዕብሪታዊ ወረራ ምክንያት እንዳይታጠፍ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ የሚቻለውን እንዲያደርግም መንግሥት አሁንም ጠይቋል።

ወገን የሆነው የትግራይ ሕዝብም ይህንን የዕብሪት ወረራ በማውገዝ ሕወሓት ከሚያስከትልበት መከራ ራሱን ነጻ እንዲያወጣም ጥሪውን አቅርቧል።

 

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.