የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በአንድነት መስራት ይኖርብናል-አቶ ግርማ የሺጥላ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 25፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአሸባሪው ህወሓት የተጋረጠብንን የህልውና አደጋ ለመቀልበስ በአንድነትና በቅንጅት መስራት አለብን ሲሉ የአማራ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ ተናገሩ፡፡
በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት የሴቶች ሊግ በወቅታዊ ጉዳዮችና ተልዕኮዎች ዙሪያ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረክ አካሒዷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ግርማ የሺጥላ÷ አሸባሪው ህወሓት የከፈተው ጦርነት እሴትን ከማውደምና ከማጥፋት ባለፈ ሀገርን የማዋረድ ተልዕኮን ያነገበ መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል ብለዋል።
ስለሆነም ነገሮችን በሰከነ መንፈስ ማጤን እና የሚስተዋሉ ተግዳሮቶችን ለይቶ እድሎችን በመጠቀሞ የተጋረጠውን የህልውና አደጋ መቀልበስ እንደሚገባ ነው ያስረዱት፡፡
አማራ የተናበበ ውስጣዊ ሰላም እንዳይኖረው የተሰራበት ህዝብ ነው ያሉት ሃላፊው÷ ይህንን ተግዳሮት እና እኩይ ስራ ለማስወገድም የክልሉ ህዝብ በአንድነት እንዲቆም መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
አማራ በአንድ አካባቢ ብቻ የሚኖር ህዝብ ባለመሆኑ በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ የሚነሱ አጀንዳዎች በሁሉም አካባቢ የሚኖረውን የአማራ ህዝብ ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው አስገንዝበዋል፡፡
አቶ ግርማ የአማራ ህዝብ ጦርነት ባይፈልግም እያንዳንዷን ደቂቃ በመጠቀም የጡት ነካሹን ጥርስ ለመስበርና ጠላት እንደ በፊቱ አፈር ልሶ እንዳይነሳ ለማድረግ እተሰራ እንደሆነ መግለፃቸውንም ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡