Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ጦርነት ለመከላከል ማንኛውንም ህጋዊ እርምጃ እንደግፋለን-የሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማህበራት ህብረት ጥምረት

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 26፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ መንግስት የተከፈተበትን ጦርነት ለመከላከል የሚያደርገውን ማንኛውንም ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፍ የሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማህበራት ህብረት ጥምረት አስታወቀ፡፡

ህብረቱ የሀገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል፡፡

ህብረቱ በመግለጫውም አሸባሪው ህወሓት ፖለቲካዊ ለውጦችን ባለመቀበል በመተው በህብረ ብሄራዊ አንድነት እሳቤ የመጣውን ለውጥ ባለመቀበል የለውጥ ጎዳናዎችን ሲያደናቅፍ መቆየቱን አንስቷል፡፡

ከለውጥ አደናቃፊነት ባለፈም ያጣውን የጭቆና አገዛዝ እና የፖለቲካ የበላይነት እመልሳለሁ በሚል ከንቱ ምኞት ተነሳስቶ ብቸኛ የሀገር እና የህዝብ ጠባቂ የሆነውን የሰሜን ዕዝ በማጥቃት ሃገሪቱን ለውጭ እና ለውስጥ አደጋ ማጋለጡን አብራርቷል፡፡

የሽብር ቡድኑ የቀረበለትን የሰላም አማራጭ ባለመቀበል አሁንም በአማራ እና አፋር ክልሎች ጦርነት መክፈቱን ያወሳው የጥምረቱ መግለጫ የኢትዮጵያ መንግስት የተከፈተበትን ጦርነት ለመከላከል የሚያደርገውን ማንኛውንም ህጋዊ እርምጃ እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡

የመግለጫው ሙሉ ሃሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከሰሜን አሜሪካ የሲቪክ ማህበራት ህብረት ጥምረት የተሰጠ ወቅታዊ መግለጫ

የህወሓት መራሹ መንግስት በኢትዮጵያ ህዝብ ላይ ለ27 ዓመታት የጫነው ኢ-ፍትሃዊነት፤ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት፤ የከፋፍለህ ግዛና ወደር የለሽ ዘረፋ ያንገፈገፈው የኢትዮጵያ ሀዝብ ይህን ከህግ በላይ መኖርን ድርጅታዊ ባህሉ ያደረገውን የፖለቲካ ቡድን ወደ ማይሸከመው ምእራፍ በመድረሱ አሽቀንጥሮ መጣሉ ይታወቃል።

ይህ አሸባሪ ቡድን የለውጥ ጎዳናውን በማደናቀፍ የኢትዮጵያን ሀዝብ ከመረገጥ እና ከመዘረፍ የሚገታውን፣ ለሀገር ክብር አንድነት ቦታ የሚሰጠውን ለዉጥ የማይቀበል መሆኑን በተግባር ሲያሳይ መቆየቱን ሁላችንም የተረዳነዉ ጉዳይ ነው።

ህወሓት ከዚህ የ“ ለውጥ አልቀበልም ባይነት እና አደናቃፊነት” አልፎ ወደ ቀድሞ የበላይነት እመለሳለሁ በሚል ከንቱ ምኞት ተነሳስቶ ብቸኛ የሃገር እና የህዝብ ጠባቂ የሆነውን የሃገር መከላከያን (የሆነውን የሰሜን ዕዝ) በማጥቃት ሀገሪቱን ለውጭ እና ለውስጥ አደጋ አጋልጧል፡፡

በአማራና በአፋር ክልሎችና ህዝብ ላይም የዕብሪት ወረራ በመፈጸም ከባድ የዘር ጭፍጨፋ በማይካድራና አካባቢዋ አድርሷል፤የትግራይን ክልል የጦር አውድማ በማድረግ ህዝቡን ታሪክ ይቅር የማይለውን ክህደትና በደል ፈጽሞበታል።

ይህ ሀቅ ግልጽ ሆኖ ባለበት በአሁኑ ወቅት የኢትዮጵያ መንግስት “ጦርነት ይብቃን፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተነጋግረን ችግራችንን እንፍታ” በሚል እምነት ለሰላም ካለው ጥልቅ ጉጉት የተነሳ፤

1. ተኩስ ማቆሙን፤

2. የዚህ ግጭት ጠንሳሾች እና ዋና ተዋናውያን መሪዎችን፣ የህዝብ ቁጣ ሳይበግርዉ ከእስር ፈትቶ መልቀቁን፤

3. ህዋሃት ለተጎዳው ህዝብ ከማደል ይልቅ እርዳታውን ለጦርነት ግብዓትነት እና የለመደውን ዘረፋ እንደሚፈጽምበት እየታውቀም ቢሆን የእርዳታ ምግብ እና ነዳጅ ያለ ችግር በብዛት እንዲገባ መድርጉን፤

4. ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰየመውን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚደንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆ በመቀበል ተደራዳሪዎችን መሰየሙን፤

5. የመከላከያ ሰራዊት፤የአማራ እና የአፋር ክልሎች የህወሓትን ብዙ ፈታኝ ትንኮሳዎችን ለሰላም ሲባል እንዲታግሱ ማድረጉን፤ … ወዘተ ወደጎን በመተው በአሁኑ ጊዜ፤ህወሓት ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት ጀምሯል፤

ለትግራይ ህዝብ ከአለም የሰላም ድርጅቶች እርዳታ የተላከውን እህል ማመላለሻ መኪናዎችን እዚያው በማስቅረት ለጦርነት ተጠቅሟል፤ የዕርዳታ ምግብ ማመላለሻ ነዳጆችን ዘርፏል፤የአለም አቀፍን የሰብአዊ መብትና የጦርነት ድንጋጌን ህግ በመጣስ ህፃናትን ለጦርንት አሰልፏል፡፡

ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የሰየመውን የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆ አልቀበልም በማለት አጠቃላይ የሰላም ሂደቱን ማደናቀፍ ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካ ህብረት ያለውን ንቀት አሳይቷል፡፡
የኤርትራን መንግስት እና ህዝብ ለመውጋት እየዛተ ነው፤የትግራይ ህዝብ ወንድሙ ከሆነው የአማራና የአፋር ህዝብ ጋር ደም ለማቃባት የቻለውን ሁሉ እያደረገ ይገኛል፡፡

የትግራይ ህዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር በሰላም የጋራ ሃገር መስርቶ ለሺህ አመታት እንዳልኖረ ሁሉ ትላንት ሀገርን እና ህዝብን ለማጥፋት የተፈጠረው ይህ ድርጅት ለትግራይ ህዝብ ብቸኛ የሰላም ዋስትና አድርጎ እራሱን በማቅረብ በድጋሜ ህዝቡን ለረሃብ እና ለክፉ ጦርነት ዳርጓል።

አሁን ባለንበት አለማቀፋዊ ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታ ህወሓት ይህን ጦርነት ለሶስተኛ ዙር መጀመር የፈለገበት ምክንያት ከላይ ከገለፅነው በተጨማሪ “የአሜሪካ ዴሞክራት ፓርቲ መራሹ መንግስት በውጪ ፖሊሲ ድክመቱ ምክንያት አለም አቀፍ ግጭቶች ተበራክቷል” የሚል የሬፐብሊካንን ጫና ለማስተንፈስ ደሃ ሃገር የሆነችው ኢትዮጵያ ላይ ማዕቀብ የመጣልም ሆነ ሌላ ጫና የማድርግ ውስጣዊ የፖለቲካ ግፊት እንዲኖር በመፈለግ እንደሆነ ጭምር እናምናለን።

ስለሆነም፤

1. የኢትዮጵያ መንግስት “ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በመነጋገር ሰላም የማስፈን” ፅኑ አቋሙ እንደተጠበቀ ሆኖ አገራችንን እና ህዝባችንን በህወሓት የተጋረጠበትን የጦርነት አደጋ በኃይል ለመከላከል የሚያደርገውን ማንኛውንም ህጋዊ እርምጃ እንደግፋለን፤

2. የኢትዮጵያ የመከላከያ ሰራዊት፣ የአማራ ልዩ ሃይል፣ የአማራ ፋኖ እና የአፋር ልዩ ሃይል ዛሬም እንደትላንቱ የህወሓትን እኩይ ጦርነት ለመመከት በየግንባሩ እየከፈለ ያለውን መስዋእት በማድነቅ፣ በውጭ የምንኖር ዳያስፖራ አካላት ሙሉ ድጋፍ እንስጣለን፤

3. ለአፍሪካ ችግር አፍሪካዊ መፍትሄ በሚል መርህ የሰላም ድርድሩን እንዲመሩ በአፍሪካ ህብረት የተሰየሙት ፕሬዚዳንት ኦሌሴጎን ኦቦሳንጆን እያደርጉ ላሉት ጥረት ሙሉ ድጋፍ እንሰጣለን፤ እኚህን አደራዳሪ ለመቀየር የሚደረግን ማንኛውንም ጫና በጥብቅ እንቃወማለን፤

ኢትዮጵያ ሀገራችን አንደነቷና ሉኣላዊነቷ ሳይደፈር ለቀጣይ ትውልድ ለማሸጋገር የተጀመረው ለውጥ እንዲሳካ አሁንም ሙሉ ምኞታችንን እንገልፃለን።

ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ተከብራ እና ተፈርታ ለዘላለም ትኑር!!!

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.