“ዲፕሎማቶች ሀገር በማዳን እንቅስቃሴ ውስጥ ኃላፊነታችንን በብቃት መወጣት ይገባናል”-አምባሳደር ብርቱካን አያኖ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ)”ዲፕሎማቶች የተሰጠንን ተልዕኮ በብቃት በመተግበር ሀገር በማዳን እንቅስቃሴ ውስጥ ኃላፊነታችንን መወጣት ይገባናል” ሲሉ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ተናገሩ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ሠራተኞችና ተጠሪ ተቋማት በወቅታዊ አገራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ዛሬ ውይይት አድርገዋል።
በውይይቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ብርቱካን አያኖ ባደረጉት ንግግር÷ ሁሉም ሠራተኞች ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያን እውነታ እንዲገነዘብ በማድረግ ለሀገራቸው ሁለተናዊ ተሳትፎ በማድረግ የበኩላቸውን ድርሻ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ተስፋዬ ይልማ እንዲሁ÷ የኢትዮጵያ መንግሥት ለሰላማዊ መፍትሔ ረጅም ርቀት መጓዙን አብራርተው፥ ለግጭቱ ዳግም መቀስቀስ ሽብርተኛው ህወሓት መንስኤ መሆኑን ጠቅሰዋል።
መንግሥት በአፍሪካ ህብረት ማዕቀፍ ሥር ለሚደረግ የሰላም ድርድር ዝግጁ መሆኑን መጠቆማቸውን ከውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽሕፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎችም መንግሥት የሰላምን አማራጭ ቀዳሚ ማድረጉ ትክክል መሆኑን ገልጸው፥ በዲፕሎማሲው ዘርፍ ለአገራቸው የሚችሉትን ለማበርከት በትጋት እንደሚሰሩ አረጋግጠዋል።