ህወሓት የትግራይን ሕዝብ ለዳግም ጦርነት መዳረጉ ሕዝባዊ ውግንና የሌለው መሆኑንና አሸባሪነቱን ዳግም የሚያሳይ ነው- የመከላከያ ሚኒስትር
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 26 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የትግራይን ህዝብ ወደ ዳግም ጦርነት ያስገባው አሸባሪው ህወሓት ህዝባዊ ውግንና የሌለውና አሸባሪነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑን የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ተናገሩ።
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር አብርሃም በላይ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፥ የተዘረጋን የሰላም አማራጭ በመናቅ ሌላ ዙር ጦርነት ማወጁ የቡድኑ ተፈጥሯዊ ባህሪ መሆኑን ጠቁመዋል።
አሸባሪው ህወሓት ከአፈጣጠሩ ጀምሮ የተለየ ሀሳብና አጀንዳ መቀበልና መስማት የማይሻ መሆኑን የሚናገሩት ዶክተር አብርሃም፥ የተለየ ሀሳብ ያለውን አካል እየገደለና እያስወገደ የመጣ አፋኝ ቡድን መሆኑንም አስረድተዋል።
አሸባሪ ቡድኑ በቀሰቀሰው ጦርነት የትግራይ ሕዝብ ክፉኛ መጎዳቱን አስታውሰው ሕዝቡ ሰላም ባለማግኘቱ ጥያቄዎችን የማቅረብ እድል መነፈጉንም ይናገራሉ።
በዚህም ቡድኑ “ልጆቻችን የት አሉ ?” የሚለውን የክልሉን ሕዝብ ጨምሮ በባለፈው ጦርነት ሕዝቡ የደረሰበትን ጉዳት ስለሚጠይቅና ዕድሜዬ ያጥራል በሚል በስጋት ውስጥ ሆኖ እየፈፀመ ያለው ወንጀል መሆኑን ጠቅሰዋል።
የትግራይ ሕዝብ የጦርነትን አውዳሚነት በታሪኩ የተረዳ፣ ሰላም ፈላጊ ሕዝብ መሆኑን ገልጸው፥ የጥፋት ቡድኑ ባለው ድብቅ ፍላጎት ሀሰተኛ ፕሮፓጋነዳ እየነዛ ሕዝቡን ለሌላ ዕልቂት እየዳረገው መሆኑን አስረድተዋል።
በዚህም ህወሓት የሀሰት ትርክትና ፕሮፖጋንዳ በመፍጠር የትግራይን ክልል ሕዝብ ለዘመናት በሠላምና በአንድነት አብሮ ከኖረው መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ለመለያየት እየሰራ መሆኑን ነው ያስረዱት።
የሽብር ቡድኑ በሰሜን ዕዝ የሀገር መከላከያ ሠራዊት ላይ ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት፥ የፌዴራሉ መንግሥት ረጅም እርቀት ተጉዞ የሠላም ጥረት ማድረጉንም ጠቅሰዋል።
አሁንም ቢሆም መንግሥት ለሠላም የዘረጋውን እጅ ሳያጥፍ ዘላቂ ሠላምና መረጋጋት እንዲመጣ እየሰራ መሆኑን አብራርተዋል።
መንግሥት የዘረጋውን የሰላም እጅ በመግፋት የትግራይን ሕዝብ በማደናገርና በማስገደድ ወደ ሌላ ዙር ጦርነት ያስገባው ተጠያቂነት እንዳይኖርበት አጀንዳ ለመፍጠር እንደሆነም አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በጀግንነቱ፣ በዲስፕሊኑና በሕዝባዊነቱ የሚታወቅ ሠራዊት እንደሆነ ገልጸው፥ ከለውጡ በኋላም በዕውቀት፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ የሚመራና ኢትዮጵያን የሚመስል ሠራዊት ስለመገንባቱ መግለፃቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
የኢፌዴሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት አሸባሪውን ህወሓት ጨምሮ ከማንኛውም ወገን የሚሰነዘርን ጥቃት በብቃት መመከት በሚያስችል ቁመና ላይ የሚገኝ መሆኑንም ሚኒስትሩ አረጋግጠዋል።