Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን ጦርነት ለመመከት ዜጎች የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪ ቀረበ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 27፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት ለመመከት ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የሀገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት ጥሪ አቀረበ፡፡

የህልውና ጦርነቱ በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ኢትዮጵያ እንደ ሀገር እንዳትቀጥል በአሸባሪው ህወሓት፣ በአልሸባብና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሀገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ነው ብሏል ምክር ቤቱ በመግለጫው፡፡

ስለሆነም ብሔራዊ ክብራችንን የሚነካ ብሎም የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል ነው ያለው ምክር ቤቱ፡፡

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የሰጠው መግለጫ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ከኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

ሀገራችን ኢትዮጵያ ተገዳ የገባችበትን የህልውና ጦርነት በጋራ ለመመከት በመላው አለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያዊን ከሕዝባቸው ጎን በቆራጥነት በመቆም የሐገርን ሉአላዊነት ለማስከበር በሚደረገው ዘመቻ የዜግነት ግዴታቸውን እንዲወጡ ጥሪያችንን እናቀርባለን::

ይህ የህልውና ጦርነት በውጭ ሀገር የምንገኘውን ኢትዮጵያውያን እንቅልፍ የነሳና ሐገራችን እንደ ሐገር እንዳትቀጥል በወያኔ ጁንታ ቡድን በአልሸባብና በሸኔ እንዲሁም በውጭ ሐገር የሚገኙ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ጠላቶች በቅንጅት የከፈቱብን ጦርነት ብሔራዊ. ክብራችንና የሚነካ የሀገራችንን ሰላም የሚያውክ በመሆኑ በእጅጉ አሳስቦናል::

ስለዚህ መንግስት በሆደ ሰፊነት ቀደም ሲል የወሰዳቸውን ቁርጠኛ የሰላም ፍላጎቶቹን በማድነቅ የሰላም ድርድሩ ውጤታማ እንዲሆን ሙሉ ድጋፍ ስንሰጥ መቆየታችን እንደተጠበቀ ሆኖ በአሸባሪነት የተፈረጀቱ ፀረ ሰላም ሐይሎች ከሰላም ይልቅ ጦርነትንና እልቂትን መርጠው የከፈቱብንን የአጥፍቶ መጥፋት ጦርነትን በጥብቅ አውግዘን መንግስት እየወሰደ ያለውን እርምጃ እንደግፋለን::

የኢትዮጵያ ዳያስፖራ የተግባር ምክር ቤት የአሸባሪውን ጁንታ ቡድን እንዲሁም አልሸባብና ሸኔን ፣ማውገዝ ብቻ ሳይሆን ለሐገር ሕልውናና ለህዝባችን ሰላምና ጥቅም ስንል ከመንግስትና እንዲሁም ከመከለከያ ሰራዊታች ጎን በመቆም የዜግነት ድርሻችንን ለመወጣት የትግባር ምክር ቤቱ ዝግጁ መሆናችንን እናረጋግጣለን::

በእርግጥ ዲያስፖራው ዛሬም ነገም ለሀገሩ ለወገኑ ድጋፉን አጠናክሮ እንደቀጠለ ቢሆንም በሐገራችን ውስጥ በተፈጠረው ሐገር የማዳን ዘመቻ በዘር በሐይማኖት በፖለቲካ እምነት ሳንከፋፈል ከስሜታዊነትና ከኩሪፊያ በመውጣት ለነገዋ ኢትዮጵያ የተሻለ ነገር ለማምጣት የተሻለችውን ኢትዮጵያ ለማየት ትግሉን የሚጠይቀውን ማንኛውንም ድጋፉ እንድናደርግ ምክር ቤታችን በድጋሚ በመላው አለም ለሚገኙ የኢትዮጵያዊያንና ለኢትዮጵያ ወዳጆች ሁሉ ጥሪ ያቀርባል::

መንግስት ኢትዮጵያን ወደ ተሻለ ከፍታ ለማድረስ ችግሮችን በውይይት በመፍታት ዘላቂ ሰላምን ለማምጣት የሐገራችንን ፖለቲካ ለማዘመን ውስጣዊ ችግሮቻችን በተገቢው መንገድ ለመፍታት ግጭቶችና የጦርነትን ውድመት እንዳይቀጥል በቁርጠኝነት ተነሳስቶ ለሀገረ መንግሥት ግንባታው መሠረት ለመጣል ፖለቲካዊ ችግሮችን በአግባቡ ፈትሾ ሁሉን ዓቀፍ ውይይትና ድርድር ማድረግ በሐገሪቱ ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጁትን ቡድኖች ወደ ዘላቂ ሰላም የጠረንጴዛ ድርድር እንዲቀመጡ ወስዶት የነበረውን የሰላም ጥረት አሁንም ወደፊትም እንዲቀጥል ምክር ቤታችን መደገፉን ይቀጥላል::

ነገርግን ከጦርነት በተሻለ ሰላምን መምረጥ ትርፋማነቱ ቢያዋጣም አሸባሪውና ጎጠኛው የጁንታው ቡድን የአማራና አፋርን ሕዝብ. በመውረር የትግራይን ሕዝብ አግተው በሰላማዊ ሕዝብና በመሰረተዊ የልማት ተቋሞች ላይ ያደረሱትን መጠነ ሰፊ ውድመት መልሰን ለማቋቋም እርብርብ በምናደርግበት ወቅት የሐገርን ሉአላዊነት አደጋ ላይ ለመጣል ለሶስተኛ ዙር የተከፈተብን ታሪክ ይቅር የማይለው ጦርነት በእጅጉ አስቆጥቶናል::

ስለዚህ 1ኛ የአማራና የአፋር ክልልን በመውረር ሲዋጉና አመራር ሲሰጡ የነበሩትን: :

እንዲሁም እድሚያቸው ለውትድርና ሞያ ያልደረሱ የትግራይ ህፃናትን በመመልመል ለጦርነት ያሰልፉትን የወያኔ ጁንታ አመራሮች ተለይተው በጦር ወንጀለኞነነትና በሐገር ክህደት ክስ ተመስርቶባቸው በአስቸኳይ ለፍርድ እንዲቀርቡ መንግስትን እንጠይቃለን::

2ኛ ሀገሪችን በገጠማት የሰላም ማጣት ችግርና ተገዳ ከገባችበት የህልውና ጦርነት በተጨማሪ የሕዝብ ሞትና የስነ ልቦና ጉዳት ሊያስከትሉ የሚችሉ የሐሰት ቅስቀሳና የፕሮፖጋንዳ ዘመቻ በሚያደርጉ ቅጥረኛ ሚዲያዎች ፣ አለአግባብ ለመበልፀግ የኢኮኖሚ አሻጥር በሚፈፅሙ ነጋዴዎች፣ በተለይ የመንግስት ሙሰኞችና ሌቦች ላይ ያለምንምንም ይቅርታ ጠንካራ እርምጃ መንግስት እንዲወስድ እናሳስባለን::

3ኛ መንግስት የሚቻለው ሁሉ ጥረት በማድረግ ለሐገር ጠቀሜታ ሲል ዘላቂ መፍትሔ የሚያመጡ አካሄዶችና አዳዲስ ስትራቴጂዎች መንደፍ አለበት: :

በተለይ ከዲያስፖራው ኮምኒቲ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዞ በጋራ የአለም አቀፉን ህብረተሰብ በተሳሳተ ፕሮፖጋንዳ የሚያውኩትን የሚዲያ ተቋማትን ተጠያቂ ለማድረግ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ለድፕሎማቶቹን. ጥብቅ መመሪያ እንዲሰጥና ለተግባራዊነቱም ልዩ ክትትል እንዲያደርግ በጥብቅ እናሳስባለን::

በመጨረሻም ምክር ቤታች ወደፊት ከሚያደርጋቸው የድጅታል ዲፕሎማሲ ትግል በተጨማሪ ጦርነቱን በአጭር ጊዜ ለመጨረስ በሚደረገው የህልውና ጦርነት የዘማቹ ሰራዊት ደጀን በመሆን ጠንካራ ድጋፍ ለመስጠት ዝግጁ መሆናችንን ለኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት እናረጋግጣለን::

ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ
ኢትዮጵያንና ሕዝቧቿን እግዚአብሔር አብዝቶ ይባርክ!!
የኢትዮጵያ ዲያስፖራ የተግባር ምክር ቤት

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.