Fana: At a Speed of Life!

የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ቅንጅት ፕሮጄክትን ወደ ተግባር ለማስገባት ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ሶማሊያ የምስራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ቅንጅት ፕሮጄክትን ወደ ተግባር ማስገባት የሚያስችል ውይይት አካሂደዋል፡፡

ውይይቱ ሶስቱ ሀገራት ወደ ቀጣይ ሒደት ለመግባት ያሉበትን ደረጃ ለመለየት፣ ፍላጎታቸውን ለማወቅ እና ፕሮጄክቱ ወደ ስራ ሲገባ ከሀገራቱ ምን ይጠበቃል በሚሉት ጉዳዮች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡

ቀጠናዊ የዲጂታል ኢኮኖሚ ቅንጅት ፕሮጀክት የአፍሪካ ቀንድ ትስስር ኢኒሼቲቭ አካል እና የመጀመሪያ ምሶሶ የሆነው ቀጠናዊ የመሠረተ ልማት ማሻሻያ አካል ነው ተብሏል፡፡

ፕሮጀክቱ በቀጠናው ያለውን የብሮድባንድ መሠረተ ልማት ክፍተት በመሙላት እና የዲጂታል አገልግሎቶችን ነጻ እንቅስቃሴን በማሳደግ የአካባቢውን ልማት መደገፍ እና የዲጂታል ገበያ ትስስርን እውን ለማድረግ ያለመ መሆኑ ተመላክቷል፡፡

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ዴኤታ ሁሪያ አሊ÷ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ በሀገራቱ መካከል የዲጂታል ገበያ ትስስር ከመፍጠር ባለፈ በኢትዮጵያ የኢንተርኔት ተደራሽነት ለማስፋት እንደሚያስችል ተናግረዋል፡፡

በዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂ ፈጣን የኢንተርኔት አገልግሎት ማዳረስ አንዱ ትኩረት የተሰጠው ጉዳይ መሆኑን የጠቆሙት ሚኒስትር ዴኤታዋ÷ ፕሮጀክቱ ወደ ስራ ሲገባ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ጉዞ ለማፋጠን ይረዳል ብለዋል።

በውይይት መድረኩ የሶማሊያ የኮሙኒኬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ጃማ ሃሰን ካሊፍ የደቡብ ሱዳን የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ምክትል ሚኒስትር ጃኮብ ማኢጁ እና የፕሮጀክቱ ኃላፊዎች መሳተፋቸውን ከሚኒስቴሩ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡

ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.