የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 80ኛ ዓመቱን አከበረ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ፣ 28፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) አንጋፋ ባለሙያዎችን እና ታላላቅ ሰዎችን ሲያፈራ የቆየው የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ 80ኛ ዓመት በዓል በዛሬው ዕለት ተከብሯል፡፡
በመርሐ ግብሩ የሥራና ክህሎት ሚኒስትር መፈሪሃት፣ የአዲስ አበባ ከተማ ሥራ አስኪያጅ አቶ ጥራቱ በየነ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የሥራ ሃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡
ወይዘሮ ሙፈሪሃት፥ ኮሌጁ በልዩ ልዩ ሙያ ያስመረቃቸው ወጣት ባለሙያዎች በሚሰጧቸው ሁሉን አቀፍ አገልግሎቶች በሀገር አቀፍ ደረጃ ለቴክኒክና ሙያ ማሰልጠኛ ተቋማት ያለን ዝቅተኛ አመለካከት መቀየር መቻሉን ተናግረዋል፡፡
የተጀመረው የለውጥ ጎዞ ሙያና በለሙያነትን የሚያከብር እና ብቁ ባለሙያዎች እንዲፈጠሩ የድርሻውን ሃላፊነት የሚወጣ ነው ያሉት ሚኒስትሯ፥ በተጓዳኝ የመምህራንንና የአሰልጣኞችን መሠረታዊ ጥያቄዎች ለመመለስ በቅንጅት ይሰራል ብለዋል ።
አቶ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው፥ ኮሌጁ ከተመሰረተበት ግዜ አንስቶ የተለየ መስፈርት በማዘጋጀት ለእጅ ሙያ ከፍተኛ ፍላጎት ያላቸውን ወጣቶች በማሰልጠን የድርሻውን በብቃት ሲወጣ መቆየቱን ጠቁመው፥ የተገኘው ስኬትም በሁሉም ረገድ ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል ብለዋል ።
የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ በዓሉን አስመልከተው ባስተላፉት መልዕክት፥ የአዲስ አበባ ተግባረ-ዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ ለሀገራችን አንቱ የተሰኙ ባለሙያዎችንና ታላላቅ ሰዎችን ሲያፈራ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
አንጋፋውና የሀገር ባለውለታው ተግባረዕድ ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ በዛሬው ዕለት የ80ኛ ዓመት በዓሉን ማክበር በመቻሉ ለመላው የኮሌጁ ማህበረሰብና ቤተሰብ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ማስተላለፋቸውን ከአዲስ አበባ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡