የብሄራዊ ቡድኑ ማሸነፍ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ አመት ስጦታ ነው – አቶ ኢሳያስ ጅራ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሸንፎ ለቻን ውድድር ማለፉ ለኢትዮጵያ ህዝብ የአዲስ አመት ስጦታ ነው ሲሉ የአትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ኢሳያስ ጅራ ተናገሩ፡፡
ርዋንዳን በማሸነፍ በታሪክ ለሶስተኛ ጊዜ ወደ ቻን ወድድር ያለፈው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ትናንት ሌሊት አዲስ አበባ ሲገባ የፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት፣ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የስራ አስፈፃሚ አባላት አቀባበል አድርገውለታል፡፡
በአቀባበሉ ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ኢሳያስ ጅራ በማሸነፋችሁ ለኢትዮጵያ ህዝብ ትልቅ የአዲስ ዓመት ስጦታ አብርክታችኋል ብለዋል።
“ከሶስት ዓመት በፊት ከውድድሩ ያስቀረንን ቡድን ጥለን ማለፋችን ትርጉሙ ብዙ ነው” ያሉት ፕሬዚዳንቱ÷ ለቻን ወድድር ላለፈው ብሄራዊ ቡድን የማበረታቻ ሽልማት እንደሚኖር እና ቀኑ በፌዴሬሽኑ ተወስኖ የሚገለፅ መሆኑን አመላክተዋል፡፡
አልጄሪያ ላይ በሚደረገው ውድድር የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ ከወዲሁ መዘጋጀት ያስፈልጋል ሲሉ አቶ ኢሳያስ ማስገንዘባቸውን ከኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡