ቢዝነስ

ጀርመን የሃይል ወጪን ለመቀነስ የ65 ቢሊየን ዩሮ ማገገሚያ ይፋ አደረገች 

By Mikias Ayele

September 05, 2022

አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን እየጨመረ የመጣውን የሃይል ወጪ ለመቀነስ የ65 ቢሊየን ዩሮ ማገገሚያ መመደቧን አስታወቀች፡፡

ጀርመን ገንዘቡን ይፋ ያደረገችው አውሮፓውያን በሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ምክንያት ከሀይል አቅርቦት ጋር እየታገሉ ባሉበት ወቅት መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡

ይፋ የተደረገው ገንዘብ በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም ከተመደቡት የሚበልጥ ሲሆን፥ ለዜጎች የነዳጅ ድጎማን ጨምሮ የግብር እፎይታና ነጻ የትራንስፖርት አቅርቦትን የሚያካትት ነው ተብሏል።

የጀርመን መራሄ መንግስት ኦላፍ ሹልዝም በማገገሚያው በተለይም ዝቅተኛ የኢኮኖሚ ገቢ ያላቸው፣ ተማሪዎች እና ጡረተኞች የድጎማ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተናግረዋል።

ከዚህ ባለፈም ወደ 9 ሺህ የሚጠጉ ከሃይል አቅርቦት ጋር የሚሰሩ ተቋማት የግብር እፎይታ ያገኛሉ ነው ያሉት።

ወደ አውሮፓ የሚገባው የሩሲያ ነዳጅ መቀነሱን ተከትሎ የነዳጅ ዋጋ በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሯል፡፡

በዚህ ሳቢያም በርካታ የአውሮፓ ሀገራት ከሃይል አቅርቦት እና ዋጋ መጨመር ጋር ተያይዞ ፈተና ውስጥ ገብተዋል ነው የተባለው።

የህብረቱ አባል ሀገራት መሪዎችም በጉዳዩ ላይ የፊታችን አርብ ይመክራሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ቢቢሲ እና አልጀዚራ በዘገባቸው አመላክተዋል።