ህወሓት የጀመረውን ጦርነት ለአንድና ለመጨረሻ ጊዜ ለማሸነፍ ከወጣቶች ከፍተኛ ርብርብ ይጠበቃል- አቶ ኡሞድ ኡጁሉ
አዲስ አበባ ፣ ነሐሴ 30 ፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ህወሓት የጀመረውን ጦርነት እንደትናንቱ ሁሉ ለአንድና ለመጨረሻ ጊዜ ለማሸነፍ በሚደረገው ርብርብ ወጣቶች የድርሻቸውን ሊወጡ ይገባል ሲሉ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ ጥሪ አቀረቡ፡፡
የጋምቤላ ክልል ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ “ለኢትዮጵያና ለአፍሪካዊ ብልፅግና የሚተጋ ትውልድ” በሚል መሪ ሀሳብ አንደኛ ቅድመ ጉባኤ ማጠቃለያ ኮንፈረንስ እያካሄደ ነው።
በኮንፍረንሱ መክፈቻ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉ እንዳሉት ከለውጡ ማግሥት አይቻልም የተባለውን ችለን እንድናሳይ የወጣቶች ሚና ከፍተኛ ነበር፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ወጣቶች ለሀገራዊው ለውጥ ዕውን መሆን ከፍተኛ መስዋዕትነት መክፈላቸውንም አውስተዋል።
የኢትዮጵያን ሰላም ለማደፍረስና ለውጡን ለማደናቀፍ የማይተኙ ኃይሎች ዛሬም ኢትዮጵያን ለማፍረስ እየሰሩ መሆናቸውን ገልፀዋል።
“ሳንወድ የገባንበትን ጦርነት እንደትናንቱ ሁሉ እጅ ለእጅ ተያይዘን ለአንድና ለመጨረሻ ጊዜ ለማሸነፍ በምናደርገው ርብርብ ወጣቶች አስተዋጽኦዋችሁን አጠናክራችሁ ልትቀጥሉ ይገባል” ሲሉም ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
በኮንፈረንሱ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኡሞድ ኡጁሉን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችና የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ወጣቶች ሊግ አባላት እየተሳተፉ እንደሚገኙ ከጋምቤላ ክልል የመንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡