በአፋር ክልል አምሥት ወረዳዎች የጎርፍ አደጋን የመከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ነሐሴ 30፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአፋር ክልል አምሥት ወረዳዎች የጎርፍ አደጋ በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት እንዳያደርስ የቅድመ መከላከል ሥራ እየተሠራ መሆኑን የኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ገለጸ፡፡
በአፋር ክልል ዱብቲ ወረዳ ከወዲሁ የቅድመ መከላከልና ግንዛቤ የማስጨበጥ ሥራ ለበጎ ፈቃደኞች እየተሠጠ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
አደጋውን መከላከል የሚያስችሉ 2 ሺህ የአሸዋ ከረጢቶች የማቅረብ ሥራ እንደሚሰራም ተነግሯል፡፡
የጎርፍ አደጋው በአፋር ክልል የሚገኙትን አሚባራ፣ አሳጊታ፣ ዱብቲ፣ ጉሌቻ እና ገዋኔ ወረዳዎች ያሰጋል ነው የተባለው፡፡
የጎርፍ አደጋው ሊከሰትባቸው ከሚችሉ አካባቢዎች ነዋሪዎችን በማስነሳት ወደተዘጋጀላቸው አካባቢዎች ሲንቀሳቀሱ ተገቢው የምግብና መሰል ድጋፎች እንደሚደረግላቸውም ተጠቁሟል፡፡
የኢትዮዽያ ቀይ መስቀል ማኅበር ከሚመለከታቸው መንግስታዊና ዓለም አቀፍ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀት የጎርፍ አደጋውን ቀድሞ መተንበይ የሚያስችል ሥርዓት በማበልፀግ የሙከራ ደረጃ ላይ እንደሚገኝ ከኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማኅበር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡