Fana: At a Speed of Life!

በኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ እና ህንድ መካከል የህዝብ ለህዝብ ግንኙነትን ለማጠናከር ያለመ ውይይት ተካሄደ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 2፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢትዮጵያ፣ ሞዛምቢክ እና ህንድ መካከል የጠነከረ የህዝብ ለህዝብ እንዲሁም የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ ውይይት ተካሄደ፡፡

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ-ጉባዔ አቶ ታገሠ ጫፎ በኢትዮጵያ እና በሁለቱ ሀገራት መካከል ስላለው  ግንኙነት፣ ተቀማጭነታቸውን አዲስ አበባ ካደረጉ ከሞዛምቢክ እና ከሕንድ ሪፐብሊክ አምባሳደሮች ጋር ተወያይተዋል፡፡

አፈ-ጉባዔው ከሞዛምቢክ አምባሳደር ጋር ባካሄዱት ውይይት÷ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የፓርላማ ለፓርላማ ግንኙነታቸውን ማጠናከር በሚችሉባቸው ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡

ግንኙነቱ ዳብሮ የጠነከረ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት እና ወዳጅነት መመሥረት በሚቻልባቸው መንገዶች ላይም ተወያይተዋል፡፡

ኢትዮጵያ እና ሞዛምቢክ የቆየ ግንኙነታቸውን በማደስ እና በማጎልበት፣ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነታቸውን ማሳደግ እንዳለባቸውም ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎቹገልጸዋል፡፡

አፈ-ጉባዔው በተመሳሳይ ከህንድ አምባሳደር ጋር የፓርላማ ለፓርላማ እና በህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች ላይ ተወያይተዋል፡፡

በተለይ ታሪካዊውን የሁለቱን ሀገራት ግንኙነት ቀደም ሲል ከነበረበት ምጣኔ-ሀብታዊ የትስስር ደረጃ በላይ ማራመድ በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ መምከራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.