Fana: At a Speed of Life!

የአፍሪካ ሀገራት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው

አዲስ አበባ፣መጋቢት 8፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በርካታ የአፍሪካ ሀገራት የኮሮና ቫረይስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው።

በቅርቡ መነሻውን ቻይና ያደረገው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ወደ ተለያዩ የዓለም ሀገራት በመዛመት ላይ ይገኛል።

አሁን ላይም በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሀገራት ቁጥር ከ160 በላይ ደርሷል።

እስካሁን በቫይረሱ 7 ሺህ 160 የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ሲያልፍ፥ በበሽታው የተያዙ ዜጎች ቁጥር ደግሞ ወደ 182 ሺህ 260 ከፍ ብሏል።

በዚህ መሰረትም በአፍሪካ ኢትዮጵያን ጨምሮ 27 የሚሆኑ ሀገራት ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆኑ ተረጋግጧል፡፡

በእነዚህ ሀገራት ውስጥም 350 ዜጎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፥ ሰባት የሚሆኑት ደግሞ ለህልፈት ተዳርገዋል።

በአህጉሪቱ የቫይረሱ ስርጭት ከቀን ወደ ቀን በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ተከትሎም ሀገራት የተለያዩ እርምጃዎችን በመውሰድ ላይ ይገኛሉ።

ደቡብ አፍሪካ የቫይረሱን ስርጭት ለመግታት በመላ ሀገሪቱ ብሄራዊ የአደጋ ጊዜ አዋጅ አውጃለች።

በአዋጁ መሰረትም ሀገሪተቱ ካሏት 72 ድንበሮች መካከል 35 የሚሆኑት ከትናንት ጀምሮ እንዲዘጉ ወስናለች።

በተጨማሪም  የአሜሪካ እና ብሪታኒያን ጨምሮ የስምንት ሀገራት  ዜጎች ወደ ሀገሪቱ እንዳይገቡ እገዳ ጥላለች።

ከዚህ ባለፈም በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉ፣ ከ100 በላይ ሰዎች የሚገኙባቸው የተለያዩ ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ እና ዜጎቿ ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ ወደ ተስፋፋባቸው ሀገራት እንዳይጓዙ አግዳለች።

ሞሮኮ በበኩሏ በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ ሲኒማ ቤቶች፣ መስጊዶች፣ካፌዎች እና ሬስቶራንቶች እንዲሁም የህዝብ ንጽህና መጠበቂያ ቦታዎች እንዲዘጉ ወስናለች።

ግብጽም ከፈረንጆቹ መጋቢት 19 ጀምሮ እስከ መጋቢት 31 ድረስ ከማንኛውንም ሀገር ወደ ሀገሪቱ ብሎም ከሀገሪቱ ወደ ሌሎች ሀገራ የሚደረግ በረራን አግዳለች።

ከዚህ ባለፈም ትምህርት ቤቶች እና ዩኒቨርሲቲዎች እንዲዘጉ እንዲሁም ሰዎች በብዛት ሊሰበሰቡባቸው የሚችሉ ዝግጅቶች እንዳይካሄዱ ውሳኔ አስተላልፋለች።

ምንጭ ፦ሬውተርስ እና ቢቢሲ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.