የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ በአፋን ኦሮሞና በትግርኛ ቋንቋ ተተረጉሞ መታተሙ ተገለፀ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 8፣ 2012 (ኤፍ.ቢ.ሲ) በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ ታትሞ በስራ ላይ የነበረው የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲ በአፋን ኦሮሞ እና በትግሪኛ ቋንቋ ተተረጉሞ መታተሙ ተገለፀ።
የኢፌዴሪ ወንጀል ፍትህ ፖሊሲው በአፋን ኦሮሞ በአማርኛና እንግሊዘኛ፤ በትግሪኛ በአማርኛና እንግሊዘኛ ቋንቋ በአንድ መጽሐፍት ታትሞ የርክክብ መከናወኑን የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ባወጣው መረጃ አስታውቋል።
በርክክቡ ላይም በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ፣ የኦሮሚያ ክልል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ ምክትል ኃላፊ አቶ ታከለ ጎሳ እና የዩ.ኤስ.ኤይድ ፍትህ ፕሮጀክት ኃላፊ ተገኝተዋል።
የኢፌዴሪ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲው በአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤይድ) የፍትህ ፕሮጀክት የገንዘብ ድጋፍ ተተርጉሞ ነው የታተመው።
በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የህግ ማርቀቅና ማስረጽ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ በላይሁን ይርጋ በዚሁ ወቅት፥ የወንጀል ፍትህ ፖሊሲውን ተፈጻሚነት ውጤታማ ለማድረግ በተለያዩ የክልል ቋንቋዎች መተርጎሙ የጎላ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
ለህትመቱ ድጋፍ ላደረገው በአሜሪካ የዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩኤስኤይድ) የፍትህ ፕሮጀክት ምስጋናቸውን አቅርበዋል።