Fana: At a Speed of Life!

በዓመት አንድ ቀን የሚውለው እድሜ ጠገቡ ገበያ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን በመንዝ ጌራ ምድር ወረዳ መስለማርያም ቀበሌ በዓመት አንድ ቀን ብቻ የሚውል ገበያ አለ፡፡

የአካባቢው ህብረተሰብ በአመት አንድ ጊዜ የሚገበያይበት ይህ ገበያ እድሜ ጠገብ መሆኑም ይነገርለታል።

“የሩፋኤል ገበያ” በመባል የሚታወቀው ይህ አመታዊ ገበያ በየአመቱ ጳጉሜን 3 ቀን ይውላል።

ዓመትን ጠብቆ የሚውለው ይህ ገበያ ታዲያ ከግብይት ባለፈ ማህበራዊ እና ሐይማኖታዊ ገጽታዎችን የተላበሰ ነው።

ከ700 ዓመታት በላይ ዕድሜ እንዳስቆጠረ የሚነገርለት “የሩፋኤል ገበያ”÷ በዘመኑ የነበሩት ነገሥታት እንዳስጀመሩት ይታመናል፡፡

በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የሚናፈቀውና የሚወደደው ይህ ገበያ፥ ነዋሪዎች ለመንግሥት ግብር እንዲከፍሉ ለማመቻቸት በማሰብ ሳይጀመር እንዳልቀረም በአፈ ታሪክ ይነገራል፡፡

የዕለቱ የገበያ ውሎ ከገበያነት ባለፈም የአመቱን ገበያ እና የሸቀጦች ዋጋ ያመላክታል የሚል ዕምነት በህብረተሰቡ ዘንድ መኖሩም ነው የሚነገረው።

በዕለቱ በገበያው ላይ ለሽያጭ የቀረበ ቁሳቁስ፣ ዕቃ፣ የቁም እንስሳት ወይም ሸቀጥ ከተወደደ÷ ዓመቱን ሙሉ ገበያው ውድ ይሆናል ይባላል።

በአንጻሩ በዕለቱ ግብይት የዋጋ ቅናሽ ከታየ፥ ቅናሹ ዓመቱን ሙሉ ይዘልቃል የሚል ዕምነት በህብረተሰቡ ዘንድ አለ።

በስፍራው በዕለቱ ከሚውለው ገበያ ባለፈ የቅዱስ ሩፋኤልን ዓመታዊና ሐይማኖታዊ በዓል ለማክበር በርካታ ምዕመናን በስፍራው በመሰባሰብ ሐይማኖታዊ ስርአት ይከውናሉ፡፡

የሩፋኤል ገበያ ሻጭና ሸማችን እያገናኘ የሰውን ዕለታዊ ፍጆታ ብሎም ፍላጎት ከመሸፈን አልፎ ሌላም ሲሳይ አለው ነው የሚባለው፡፡

መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ለአቅመ አዳምና ሔዋን የደረሱ ወጣቶች በትዳር ተጣምረው ለመኖር የሩፋኤል ገበያን እንደ መልካም አጋጣሚ ይጠቀማሉ፡፡

እናም በእይታ የተፈላለጉ ወጣቶች ከገበያው ዕቃ ሸምተው፥ ቀልባቸው ያረፈበትን አጭተው፤ ውሃ አጣጫቸውንም ይዘው ይመለሳሉ።

የወረዳው ባህልና ቱሪዝም ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ወይዘሮ ቅመም አሽኔ ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ “አካባቢውን የቱሪዝም መዳረሻ ለማድረግ ከደብረብርሃን ዩኒቨርሲቲ ጋር በጋራ እየተሠራ ነው”፡፡

የአካባቢውን ታሪካዊነት የሚያሳዩ የቤተ መንግሥት ፍርስራሾች እና ጥንታዊ ቅርሶች መኖራቸው አካባቢውን ለማልማት መልካም ዕድል ነው ያሉት ኃላፊዋ÷ የሰሜንሸዋ ዞንም አስፈላጊውን ሁሉ እገዛ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በገበያው ዕለት የአካባቢው ነዋሪዎችን ጨምሮ ከአጎራባች ወረዳዎች የሚሰባሰቡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች አንድም ለመጎብኘት አንድም ደግሞ ለመገበያየት በቦታው እንደሚገኙ ወይዘሮ ቅመም ይናገራሉ፡፡

በገበያው÷ የቁም እንስሳት፣ የእርሻ መሣሪያዎች፣ የፋብሪካ እና የግብርና ምርት ውጤቶች እንዲሁም የእንስሳት ተዋጽኦ ይቀርባሉ፡፡

እንደ ኃላፊዋ ገለጻ÷ አካባቢው የመንገድ፣ ኤሌክትሪክ እና እንደ ውሃ ያሉ መሰረተልማቶች ያልተሟሉለት በመሆኑ በቀጣይ ከባለድርሻ አካላትና ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት ለመሥራት ታቅዷል፡፡

በታለ ማሞ

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.