Fana: At a Speed of Life!

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላ የማየት ራዕይን ለማሳካት በቅንጅት ይሰራል – ኢንጂነር አይሻ መሐመድ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት አመቱ ኢትዮጵያ በምግብ ራስን ችላ የማየት ራዕይን ለማሳካት ከዘርፉ ባለሃብቶች ጋር በጋራ እንደሚሰራ የመስኖ እና ቆላማ አካባቢ ሚኒስትር ኢንጂነር አይሻ ሙኃመድ ገለጹ፡፡

ኢንጂነር አይሻ አዲስ አመትን አስመልክቶ ባስተላለፉት የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት÷ አዲሱ አመት ሰላም የሰፈነባት፣ ፍቅር የሚነግስበት እና የተጀመሩ የልማት ስራዎች የሚሳኩበት እንዲሆን ተመኝተዋል ፡፡

2014 ዓ.ም በብዙ ፈተናዎች ውስጥ በማለፍ ብዙ ነገሮች የተሳኩበት እንደነበር ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ ገልጸዋል።

“በአዲሱ አመትም ችግሮች ተሸግረንያሰብናቸውን በጎ ስራዎች የምናሳካበት ፣ የጀመርነውን የምንጨርስበት እና ሰላም የሚሰፍንበት እንዲሆን እመኛለሁ” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ ሰፊ የመሬት እና እምቅ የውሃ ሃብት ያላት ሀገር መሆኗን በመጥቀስም፥ “እነዚህን የመስኖ አለኝታዎች በአግባቡ በማልማት በተቀናጀ አግባብ ወደ ልማት የምናሸጋግርበት ጊዜ” እንዲሆን እመኛለሁም ነው ያሉት።

ከሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ጋር ሆነው በግብርና ሜካናይዜሽን እና ኢንቨስትመንት ለተሳተፉ የሀገር ውስጥም ሆኑ የውጭ ባለሃብቶች አስፈላጊው ሁሉ እገዛ እንደሚደረግም ሚኒስትሯ አረጋግጠዋል፡፡

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን ችላ የማየት ራዕይን ለማሳካት ከዘርፉ ባለሃብቶች ጋር በጋራ እንሰራለንም ነው ያሉት ሚኒስትሯ፡፡

የአርብቶ አደሮችን የኢኮኖሚ ተጠቃሚነት በማረጋገጥ ለሀገር ኢኮኖሚ እድገት ገንቢ አስተዋጽኦ እንዲያበረክቱ የሚያስችሉ ስራዎች እንደሚሰሩም አስረድተዋል።

“አዲሱ አመት በአንድነት ሆነን ሀገራችን ለማፍረስ የሚጥሩ ሃይሎችን በሙሉ የምናሸንፍበት፤ ህልማቸው እንዳይሳካ የምንሰራበት ዘመን እንዲሆን እመኛለሁ” ሲሉም መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

በአመለወርቅ ደምሰው

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.