Fana: At a Speed of Life!

የሠላም ቀን በክልሎች ተከበረ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ዛሬ ሀገር አቀፍ የሠላም ቀን “ሠላም ለኢትዮጵያ” በሚል መሪ ቃል  ተከበረ፡፡

 

ክልሎችም ቀኑን በተለያዩ መርሐ-ግብሮች አክብረዋል፡፡

 

በአፋር ክልልም  ቀኑን ምክንያት በማድረግ  የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አወል አርባን ጨምሮ የተለያዩ የመንግስት ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት  “ሠላም ለኢትዮጵያ” የተሰኘ የሠላም ሐውልት ሠመራ  አደባባይ ላይ ተተክሏል፡፡

 

በተመሳሳይ በሐረሪ ክልል የሠላም ቀንን ምክንያት በማድረግ የ10 ኪሎ ሜትር የሩጫ ውድድር ተካሂዷል፡፡

 

በውድድሩ ከ1 እስከ 3ኛ ላጠናቀቁ ተወዳዳሪዎች የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ ኦርዲን በድሪ  ሽልማት አበርክተዋል፡፡

 

ስፖርት ሠላምን ለማጠናከር ያለው ሚና የጎላ በመሆኑ የሠላም ቀንን በተለያዩ ስፖርታዊ ውድድሮች ማክበር እና የሩጫ ውድድሩን ማዘጋጀት አስፈላጊ ሆኖ መገኘቱ  ተገልጿል።

 

የ”ሠላም ቀን”በደቡብ ክልል ዲላ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች ተከብሯል።

 

በደቡብ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመልካም አስተዳደር ዘርፍ  አስተባባሪና የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ÷ ቀኑ ሲከበር የሰላም ምሶሶ መትከል የዕለቱ ዐቢይ ጉዳይ መሆኑን ተናግረው ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋነኛ የሠላም ማስተላለፊያ መንገድ መሆኑን አውስተዋል።

 

የሠላም ቀን በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ በክልሉ የጸጥታ ቢሮ አዘጋጅነት መከበሩ ተገልጿል፡፡

 

በመርሐ ግብሩ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ መሃመድ ፣ የክልሉ ሠላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሙበሽር ድባድ ራጌ፣ የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር መሀመድ ሀሰን አህመድ እና ሌሎች የክልሉ ጸጥታ አካላት አመራሮችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች ተገኝተዋል ።

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.