በበጀት አመቱ 27 የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በበጀት አመቱ 27 የመስኖ ፕሮጀክቶች እንደሚገነቡ የመስኖና ቆላማ ሚኒስትር ዴዔታ ዶክተር ብርሃኑ ሌንጂሶ ገለጹ።
ሚኒስትር ዴዔታው ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ፥ የመስኖ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የምግብ ዋስትናን ከማረጋገጥ አንጻር መስኖ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዳለውም አስረድተዋል፡፡
የመስኖና ቆላማ ልማት በሚኒስቴር ደረጃ ከተቋቋመ በኋላ ባለፉት 10 ወራት ባከናወናቸው ተግባራት 17 የመስኖ ፕሮጀክቶችን ተቀብሎ ወደስራ ማስገባቱን ገልጸዋል፡፡
ተጀምረው በጥገና ምክንያት የቆሙ ፕሮጀክቶችን ጥገናቸውን አጠናቆ ወደስራ እንዲገቡ የማድረግ ስራ መሰራቱንም ነው ያነሱት፡፡
በዚህም 157 ሺህ ሄክታር ውሃ ገብ መሬት ለግብርና ስራ ማቅረብ መቻሉንም አመላክተዋል።
በተለይም የመስኖ ልማቱ በስንዴ ምርታማነት ላይ የሚታዩ ለውጦችን ማምጣት መቻሉንም ነው ያመላከቱት።
በቀጣይ የተጀመሩ ፕሮጀክቶች ሲጠናቀቁም ከ500 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ ለመስኖ ልማት ለማልማት ታስቧልም ነው ያሉት።
ከዚህ ጋር ተያይዞም በበጀት አመቱ 27 የመስኖ ፕሮጀክቶች ይገነባሉ ያሉት ሚኒስትር ዴዔታው ፥ 29 የሚሆኑት ደግሞ የጥናትና ዲዛይን ስራ እንደሚሰራላቸው አውስተዋል።
በሂደቱ እንደ ችግር ያጋጠመውን የካሳ ግመታና ጥያቄን በቋሚነት መፍታትም አስፈላጊ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የሲሚንቶ ችግርም ሌላኛው የዘርፉ ፈተና መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡
አክለውም የመስኖ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ኢትዮጵያ ያለባትን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ እንደሚያግዝ ተስፋ ተጥሎበት እየተሰራ መሆኑንም ነው የገለጹት፡፡
ኢትዮጵያ በተፈጥሮ ያላትን ሃብት ተጠቅማ ለመልማት በምትሰራው ስራ የመስኖ ልማቱ አንዱ ተግባር ሲሆን ፥ ዘርፉን ለማጠናከር ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጋራ ሊሰሩ ይገባል ብለዋል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!