የኦሮሚያ ክልል ለመከላከያ ሰራዊት ከ101 ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ድጋፍ አደረገ
አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 3፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) የኦሮሚያ ክልል ለመከላከያ ሠራዊት የአዲስ ዓመት በዓልን ምክንያት በማድረግ ከ101ነጥብ 3 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የዓይነት ድጋፍ አድርጓል፡፡
ድጋፉን በምክትል ርዕሰ መስተዳደር ማዕረግ የገቢዎች ቢሮ ሃላፊ ወይዘሮ መስከረም ደበበ ለመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ አስረክበዋል።
ድጋፉ በክልሉ ውስጥ ከሚገኙ ከሁሉም ከተሞችና ዞኖች የተሰበሰበ መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
የተደረገው ድጋፍ 1 ሺህ 329 ሰንጋዎች፣ 200 በጎችና ፍየሎች፣ ምግብ ነክ ምግቦችና የጽዳት መጠበቂያዎችን ያካተተ መሆኑ ተገልጿል፡፡
ድጋፉን ያስረከቡት ወይዘሮ መስከረም ደበበ፥ የሰላም እጆች ተዘርግቶለት ጦርነት የከፈተውን አሸባሪው ህወሓትን በመመከት የሀገር ሉዓላዊነት ለማስከበር በግንባር እየተዋደቀ ለሚገኘው የጀግናው የሀገር መከላከያ ሰራዊት በዓልን እንዲያከብር በማሰብ መሆኑን ተናግረዋል።
ድጋፋ የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም ያሉት ሀላፊዋ፥ ጦርነቱ እስኪቀለበስ ደረስ ክልሉ ከሰራዊቱ ጀርባ ደጀን ሆነን እንቀጥላለን ብለዋል።
የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታ ማርታ ሉዊጂ በበኩላቸው፥ የኢትዮጵያ ህዝብ በሁሉም ግንባር ተሰልፎ ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ደጀንነቱን እያሳየ መሆኑን ተናግረዋል።
በዛሬው እለት ለተደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበው፥ የሚደረጉ ድጋፎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉም አሳስበዋል።
በመራኦል ከድር
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!