Fana: At a Speed of Life!

ከአሸባሪው ትህነግ ተልዕኮ ተቀብለው የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ 19 የሽብር ቡድን አባላት በቁጥጥር ስር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 4፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) ከአሸባሪው ትህነግ ተልዕኮ ተቀብለው በአዲስ አበባ እና አካባቢው የህዝብን ሰላም ሲያውኩ የነበሩ 19 የሽብር ቡድን አባላት በተደረገው ከፍተኛ ዘመቻ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል አስታወቀ፡፡

ጠላቶች አዲስ አበባን የሽብር ማዕከል እናደርጋለን ብለው በአደባባይ ከፎከሩበት ጊዜ ጀምሮ እኩይ ተግባራቸውን ለመፈፀም ያላደረጉት ሙከራ እንዳልነበረ የቅርብ ጊዜ ትውስታ መሆኑን ፖሊስ ገልጿል፡፡

በልዩ ልዩ የተሽከርካሪ የውስጥ አካላት ጭምር ድብቅ ቦታዎችን እያዘጋጁ ከነብስ ወከፍ እስከ ቡድን የጦር መሳሪያዎችን ወደ ከተማው ለማስገባት ያደረጉት ሙከራ በህብረተሰቡ ተባባሪነትና በፀጥታ ኃይሉ ብርቱ ጥረት እንደከሸፈም ነው ያስታወቀው፡፡

ካለፉት ሁለት ወራት ወዲህ ደግሞ ጠላቶቻችን ስልታቸውን በመቀየር በአዲስ አበባ እና በዙሪያዋ ባሉ ከተሞች ህዝቡ የደህንነት ዋስትና እንዳይሰማው በማቀድ በንፁሃን ላይ ከባድ የዘረፋ እና የውንብድና ወንጀሎችን ጨምሮ አሰቃቂ ግድያን ሲፈፅሙ ቆይተዋል ተብሏል፡፡

 

የአዲስ አበባ ፖሊስ ከመከላከያ ሠራዊት፣ ከፌደራል ፖሊስ፣ ከብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎትና ከኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ ጋር በመሆን ባደረገው የተቀናጀ ዘመቻ ነው የወንጀል ቡድኖች በቁጥጥር ስር መዋላቸው የተገለጸው፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በተለምዶ ራይድ ተብለው የሚጠሩ ተሽከርካሪዎች ላይ ተሳፋሪ መስለው ከገቡ በኋላ ወደ ሰዋራ ስፍራ ወስደው በአሽከርካሪዎቹ ላይ የግድያ እና የውንብድና ወንጀሎችን ሲፈፅሙ የቆዩ ናቸውም ተብሏል፡፡

ተጠርጣሪዎችን ጥምር የፀጥታ ሃይሉ ባደረገው ብርቱ ክትትል በቁጥጥር ስር አውሎ ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ፖሊስ ገልጿል፡፡

በሌላ በኩል በጦር መሳሪያ የተደገፈ ዘረፋ፣ የመግደል ሙከራ እና የውንብድና ወንጀሎችን በየካ፣ በለሚኩራ፣ በቦሌ እና በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተሞች ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ሲፈፅሙ የቆዩም ይገኙበታል ነው ያለው ፖሊስ፡፡

ግለሰቦቹ ስለፈፀሙት ወንጀል በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው ከመሆኑም ባሻገር ወንጀል መፈፀማቸውን አምነው ቦታውንና አፈፃፀሙን ለፖሊስ መርተው አሳይተዋል ነው የተባለው፡፡

12 ልዩ ልዩ ተሽከርካሪዎች፣ ለዕኩይ አላማ ማስፈፀሚያ ይጠቀሙባቸው የነበሩ የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነዶች እና ልዩ ልዩ የፀጥታ አካላት የደንብ ልብስም ተይዘዋል፡፡

ሽብርተኛው የትህነግ ቡድን ከተማ ላይ ሽብር ለመፍጠር የሽብር ቡድኑን አባላት መልምሎ በድብቅ ወደ አዲስ አበባ ላስገባቸው ተላላኪዎቹ ልዩ ልዩ የጥፋት ተልዕኮ ሰጥቶ አሰማርቶ እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ህዝቡ ተባባሪነቱን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪ መቅረቡንም ከአዲስ አበባ ፖሊስ የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.