Fana: At a Speed of Life!

የወርቅ ጌጣጌጦችን በመዝረፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ

አዲስ አበባ፣ ጳጉሜን 5፣ 2014 (ኤፍ ቢ ሲ) በቡድን ተደራጅተው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በመልበስ የወርቅ ጌጣጌጦችን በመዝረፍ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ሥር ዋሉ፡፡
 
በሞጆ ከተማ ከአንድ ግለሰብ የወርቅ መሸጫ ሱቅ 49 ግራም የሚመዝኑ የወርቅ ጌጣጌጦችን ዘርፈው ከአካባቢው የተሰወሩ ተጠርጣሪዎች በህብረተሰቡ ጥቆማ እና በፖሊስ ክትትል በቁጥጥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
 
በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ የታክቲክ ወንጀል ምርመራ ምክትል ዋና መምሪያ ኃላፊ ረዳት ኮሚሽነር ብርሃኑ አበበ÷በቡድን ተደራጅተው በተለያየ ጊዜ የፖሊስን የደንብ ልብስ በመልበስ ዘረፋ የሚያካሄዱ ግለሰቦች እየተበራከቱ መምጣታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
 
ይህ ተግባር የጸጥታ ኃይሉን ስም ለማጠልሸትና የጠላትን ዓላማ ለማሳካት ሆን ተብሎ የተፈፀመ መሆኑን ነው የገለጹት፡፡
 
ድርጊቱ የተፈፀመው በሞጆ ከተማ ሆኖ ሳለ በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በአዲስ አበባ ከተማ ፒያሳ ወርቅ ቤት እንደተፈመ የተገለፀው ስህተት መሆኑንም አንስተዋል።
 
ፖሊስ ለደንብ ልብሱና ለዓላማው ልዩ ክብርና ትኩረት ሰጥቶ የሚሰራ መሆኑን የተናገሩት ረዳት ኮሚሽነሩ÷ የማዕረግ የደንብ ልብሱን ለብሶ ማንም ሰው ስሙን ማጠልሸትና ማጉደፍ እንደሌለበትም ጠቁመዋል፡፡
 
የወንጀል ቡድኖቹ ከሌሎች ግብረ-አበሮች ጋር በመመሳጠር ሞጆ አካባቢ በአንድ ወርቅ ቤት ወርቅ ገዥ መስለው ፖሊስ ያልሆነውን ሰው የፖሊስን የደንብ ልብሰ በማልበስ ሽፋን እንዲሰጥ በማድረግ ሌሎቹ ወርቁን ዘርፈው እንዲወጡ መደረጉን ረዳት ኮሚሽነሩ ገልጸዋል፡፡
 
ሕብረተሰቡ በሰጠው ጥቆማ ላይ ተመስርቶ ፖሊስ ባደረገው ብርቱ ክትትል በዘረፋው ላይ የተሳተፉ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሚገኝ ከፌዴራል ፖሊስ ያገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.