ጀርመን ለዩክሬን የጦር መሣሪያ በማቅረብ ቀይ መስመር አልፋለች- ሩሲያ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 2፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ጀርመን ለዩክሬን የተለያዩ ጦር መሣሪያዎችን በማቅረብ ረገድ ቀይ መስመር አልፋለች ስትል ሩሲያ ወቀሳ አወገዘች፡፡
በጀርመን የሩሲያ አምባሳደር ሰርጌይ ኒቻዬቭ እንዳስታወቁት÷ በርሊን ዘመኑን የዋጁ እና ጅምላ -ጨራሽ የጦር መሳሪያዎችን ለዩክሬን መንግስት እያስታጠቀች ነው፡፡
በዚህም በሩሲያ ወታደሮች ላይ ጥቃት እንዲከፈት ከማድረግ ባሻገር በዶንባስ ንጹሃን ዜጎች እንዲገደሉ አድርጋለች ሲሉ ነው ጀርመንን የኮነኑት፡፡
ድርጊቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጠናቀቅ እና የጀረመኑ ናዚ ሶቪዬት ኅብረትን ከወረረ በኋላ ለዓመታት የተካሄደውን እርቀ ሰላም ግምት ውስጥ ያላስገባ ነው ብለዋል፡፡
ከዚህ ባለፈም በድርጊቱ በርሊን እንደ ዋሽንግተን እና ሌሎች የኔቶ አባል ሀገራት “የጦር መሣሪያ ወደ ግጭት ቀጠና አለመላክ” በሚል የነበራትን ፖሊሲ መጣሷን አመላክተዋል፡፡
ከዚህ አንፃርም ጀርመን ከሩሲያ ጋር ለዘመናት የገነባችውን የሁለትዮሽ ግንኙነት ለማዛባት የተናጠል እርምጃ ጀምራለች ሲሉ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡
ስለሆነም በርሊን በቀጣይ በሩሲያ የውስጥ ጉዳይ ላይ የምታደርገውን አላስፈላጊ ጣልቃ ገብነት እንድታቆም ነው አምባሳደሩ ያሳሰቡት፡፡
በሌላ በኩል አሜሪካ እና ምዕራባውያን በሩሲያ ላይ የጣሉት ዘርፈ ብዙ የኢኮኖሚ ማዕቀብ ለሞስኮ መልካም ትሩፋት ይዞ እንደመጣ መናገራቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡