Fana: At a Speed of Life!

ዩክሬን በካርኮቭ ላካሄደችው ዘመቻ አሜሪካ ድጋፍ ማድረጓን ሴናተር ዋርነር አረጋገጡ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሩሲያ – ዩክሬን ጦርነት ዩክሬን ከሰሞኑ ባደረገችው የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ ለተገኘው “ሥኬት” አሜሪካ እና አጋሮቿ ድጋፍ ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡

አሜሪካ እና አጋሮቿ የሆኑት የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ዩክሬን በካርኮቭ ለፈጸመችው የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ድጋፍ በማቅረብ ረገድ ትልቅ ድርሻ እንደነበራቸው የአሜሪካው ሴናተር ማርክ ዋርነር ለሲ ኤን ኤን ተናግረዋል፡፡

በተለይም አሜሪካ እና ብሪታኒያ የሥለላ መረጃዎችን ከዩክሬን ጋር በመለዋወጥ ኪየቭ በካርኮቭ በወሰደችው የመልሶ-ማጥቃት እርምጃ “ትልቅ ስኬት” እንድትቀዳጅ ከፍተኛ ሚና ማበርከታቸውን ሴናተሩ ገልጸዋል፡፡

የአሜሪካ ሴኔት የስለላ ኮሚቴ ኃላፊ የሆኑት ማርክ ዋርነር ÷ የአሜሪካ እና የብሪታንያ የስለላ ጥምረት ኃይሎች ከዩክሬን ጋር እየሠሩ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

ይህ ዓይነቱ ትብብር የሀገራቱን ወታደራዊ ጥንካሬ እንደሚያሳይም ነው የጠቆሙት፡፡

አሜሪካ እና የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል ሀገራት ለዩክሬን ወታደራዊ ኃይል ያልተቋረጠ እና ትልቅ የወታደራዊ መሣሪያ አቅርቦት ድጋፍ ሲያደርሱ እንደነበርም በማድነቅ አንስተዋል፡፡

ባሳለፍነው ሐሙስ የዩክሬን ወታደራዊ ኃይል በካርኮቭ የመልሶ-ማጥቃት እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ሩሲያ ወታደራዊ ኃይሏን ከሰሜን ምሥራቃዊ ዩክሬን ማስወጣቷን የሀገሪቷ መከላከያ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡

መከላከያ ሚኒስቴሩ በዶኔስክ ያለውን ወታደራዊ ኃይል ለማጠናከር በማሰብ ውሳኔው መወሰኑንም በወቅቱ መግለጹ አይዘነጋም።

የሩሲያ መከላከያ ኃይል መውጣቱን ተከትሎ የዩክሬን ወታደሮች ድል አድርገናል በሚል ደስታቸውን መግለጻቸውን አር ቲ ዘግቧል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.