Fana: At a Speed of Life!

የደብረታቦርን የውኃ ችግር ለመፍታት የማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፣ መስከረም 3፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የደብረታቦር ከተማን የውኃ ችግር ለመፍታት በ134 ሚሊየን ብር የማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተሠራ መሆኑን የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ አስታወቀ፡፡

የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ማማሩ አያሌው ለፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት እንደገለጹት÷ በከተሞች የሚታየውን የውኃ አገልግሎት ችግር ለማስተካከል ቢሮው የተለያዩ ሥራዎችን እያከናወነ ነው።

በደብረታቦር ከተማ የሚስተዋለውን የንፁህ መጠጥ ውኃ ችግር ለመፍታት በ134 ሚሊየን ብር ወጪ የማስፋፊያ ፕሮጀክት እየተሠራ ሲሆን÷ ለዚህም በደብረ ታቦር ከተማ አስተዳደር እና በአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ መካከል ስምምነት ተፈርሟል፡፡

ፕሮጀክቱ በስድስት ወራት የሚጠናቀቅ ሲሆን፥ ግንባታው ሲጠናቀቅ የከተማውን የውሃ ችግር በ30 በመቶ ይቀንሳል ተብሎ ይጠበቃል።

የደብረታቦር ከተማ የውኃ ሽፋን 11 በመቶ ሲሆን÷ የከተማውን የውኃ ችግር በዘላቂነት ለመፍታት አማራጭ የውኃ ፕሮጀክት ጥናቶች እየተሠሩ መሆኑ ተጠቁሟል፡፡

በ2014 ዓ.ም የክልሉ የውኃ መጠጥ ሽፋን በ2 ነጥብ 3 በመቶ እንደተሻሻለ አስታውሰው÷ በተያዘው በጀት ዓመትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ይሠራል ብለዋል፡፡

የአማራ ክልል ውኃና ኢነርጂ ቢሮ ከኬር ኢትዮጵያ ጋር በመተባበር የደብረ ታቦር ከተማን የውኃ እጥረት ለመቅረፍ የሚያግዝ የ12 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል፡፡

በምናለ አየነው

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.