Fana: At a Speed of Life!

የኢኮኖሚ አሻጥሮችን ለመቅረፍ ዘላቂ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ ይገባል- የዘርፉ ባለሙያዎች 

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የዜጎች ህይወት ላይ ጫና እያሳደሩ የቀጠሉትን የምጣኔ ሃብት አሻጥሮች ለመቅረፍ ዘላቂ ስራዎች ላይ ትኩረት ማድረግ እንደሚገባ የዘርፉ ባለሙያዎች ተናገሩ፡፡

አምራችና አቅራቢዎች ከተጠቃሚው ጋር በቀጥታ የሚገናኙበት መንገድ ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ነው የምጣኔ ሃብት መምህርና ተመራማሪዎች የተናገሩት፡፡

የኢኮኖሚ አሻጥሩን በጊዜያዊነት ከሚያቀሉ ጥብቅ ቁጥጥር ስራዎች ባሻገር ፣ ኢንቨስትመንትን በተሻለ ማበረታታት እንደሚገባም ባለሙያዎቹ አስረድተዋል፡፡

ዘርፉን የመቆጣጠር ሃገራዊ ሃላፊነት ያለባቸው መንግስታዊ ተቋማት መፈተሽ እንዳለባቸውም ነው ባለሙያዎቹ የጠቆሙት፡፡

ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ቆይታ ያደረጉትና በአዲስ አበባ ዪኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህር ዶክተር ንጉሴ ስሜ፥ አምራች እና አቅራቢዎች በቀጥታ ከተጠቃሚው ጋር የሚገናኙበት ጠንካራ አሰራር ሊዘረጋ ይገባል ብለዋል፡፡

የኢኮኖሚ አሻጥሮች በዜጎች ኑሮ ላይ ከፍ ያለ ጫና እያሳደሩ መሆኑን ያነሱት ዶክተር ንጉሴ፥ ከቁጥጥር ስራዎች ባሻገር ምርትና አቅርቦት ስራ ላይ የተሰማሩ አካላትን ማበረታታት እንደሚያስፈልግም አብራርተዋል፡፡

ከዶክተር ንጉሴ ሃሳብ ጋር የሚስማሙት በወራቤ ዩኒቨርሲቲ የምጣኔ ሃብት መምህሩ መሃመድ ኢሳ ትክክለኛ የቁጥጥርና ክትትል ስራዎች ሊተገበሩ እንደሚገባ አንስተዋል፡፡

በዘርፉ ሀገራዊ ሃላፊነት ያለባቸው ተሿሚዎች አቅምን መንግስት በአግባቡ ሊፈትሽ እንደሚገባም የምጣኔ ሃብት መምህራኑ ሃሳባቸውን አካፍለዋል፡፡

 

በአወል አበራ

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.