ህብረተሰቡ ከሕጋዊ አሠራር ውጪ ቀረጥና ታክስ ነጻ አስፈቅደናል ከሚሉ አካላት እንዲጠነቀቅ ገንዘብ ሚኒስቴር አሳሰበ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ህብረተሰቡ ከሕጋዊ አሠራር ውጪ ማህበር እናደራጃለን፣ ቀረጥና ታክስ ነጻ አስፈቅደናል ወይም እናስፈቅዳለን ከሚሉ አካላት እንዲጠነቀቅ ገንዘብ ሚኒስቴር አሳስቧል፡፡
ሚኒስቴሩ በሰጠው ማብራሪያ በመዲናዋ በማገልገል ላይ የሚገኙ የላዳ ታክሲዎች በአዲስ እንዲተኩ በማድረግ ባለንብረቶቹን በተሽከርካሪዎቹ እርጅና ምክንያት ከሚደርስባቸው ከፍተኛ የነዳጅና የመለዋወጫ ወጪ ለማዳን አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን አስታውሷል።
ከዚህ ባለፈም በገበያ ላይ ተወዳዳሪ ሆነው በመሥራት ተጠቃሚ እንዲሆኑ፣ የአካባቢ ብክለትን ለመቀነስ፣ የከተማዋን ገፅታ ለማሻሻል እና የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን በማሰብ ያገለገሉ ላዳዎችን የሚተኩ አዳዲስ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነጻ እንዲሆኑ መደረጉን ጠቅሷል።
የታክሲ ተሽከርካሪዎች የቀረጥና ታክስ ነጻ ጥያቄዎች አቀራረብና አፈቃቀድን በተመለከተ በተደነገገው መሠረት የታክሲ ተሽከርካሪዎች ቀረጥና ታክስ ነጻ ጥያቄዎች የሚስተናገዱት ያገለገሉ ላዳ ታክሲዎችን የሚተኩት÷ ተሽከርካሪዎች ሙሉ በሙሉ (በከፊል) ተበትነው ወደ ሀገር ገብተው በሀገር ውስጥ ተገጣጥመው ሲቀርቡ ብቻ መሆኑ ገልጿል፡፡
አዲስ የታክሲ ማኅበራትን በሚመለከት ትኩረት የሚያደርገውም÷ የትራንስፖርት ዘርፉን ፍላጎት ሆኖ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር በሚያዘጋጀው ሀገር አቀፍ የትራንስፖርት ፖሊሲና ስትራቴጂ ብቻ የሚወሰን መሆኑንም ማብራሪያው አመላክቷል፡፡
በዚህም መሰረት የሚቀርቡ ጥያቄዎች የሚስተናገዱት ለዚሁ ዓላማ በወጣው መመሪያ ቁጥር 70/2013 መሰረት በማድረግ ብቻ ነው ብሏል፡፡
በዚህ መመሪያ ግልፅ የጥያቄ አቀራረብና የአፈቃቀድ ስርዓት መደንገጉንና በተለይም በመመሪያው አንቀፅ 10 መሰረት ለታክሲ አገልግሎት የሚውሉ የተሽከርካሪ ቀረጥና ታክስ ነጻ ጥያቄዎች መቅረብ የሚችሉት በሚከተለው መንገድ ብቻ መሆኑን ገንዘብ ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
የክልል መንግስታት፣ የከተማ አስተዳደሮች እና የፌዴራልና የመንግስት መስሪያ ቤቶች ለታክሲ አገልግሎት የሚውሉ ተሽከርካሪዎች ከቀረጥና ታክስ ነፃ የሚገዙትን ተሽከርካሪዎች የሚፈልጉ የታክሲ አገልግሎት ሰጪ ማህበራት ጥያቄ ከድጋፍ ደብዳቤ ጋር ለትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር ሲላክ፤
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የታክሲ ማህበሩን የግብር ከፋይ መለያ፣ የንግድ ምዝገባ ሰርተፊኬት፣ የተሽከርካሪዎቹን ሊብሬ እና ሌሎች አስፈላጊ መረጃዎችን በማያያዝ ለገንዘብ ሚኒስቴር ሲልክ፤
የገንዘብ ሚኒስቴርም የቀረበውን ጥያቄ አግባብነት እና ማስረጃዎች ከመረመረ በኋላ የቀረጥ ነፃ መብቱን በመስጠት ለጉምሩክ ኮሚሽን ሲልክ መሆኑን አብራርቷል፡፡
ከዚህ መመሪያ ውጭ የሚቀርቡ ጥያቄዎች የህግ መሰረት የሌላቸው በመሆኑ ተቀባይነት የሌላቸውና ከመመሪያው ውጪ የሚቀርቡ የታክሲ ተሽከርካሪ ቀረጥና ታክስ ነጻ ጥያቄዎች ከገንዘብ ሚኒስቴር እውቅና ውጭ መሆናቸውን በማወቅ ህብረተሰቡ ከተጠቀሰው ህጋዊ አሰራር ውጪ ማህበር እናደራጃለን፣ ቀረጥና ታክስ ነጻ አስፈቅደናል ወይም እናስፈቅዳለን ከሚሉ አካላት ራሱን እንዲጠብቅ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግሥት የትራንስፖርት ዘርፉን ለማዘመን እንዲሁም ለረጅም ጊዜ አገልግሎት በመስጠት ላይ የሚገኙ ‹‹ላዳ ታክሲ›› ተሽከርካሪዎች በአዲስ ተሽከርካሪዎች የሚተኩበት መመሪያ ቁጥር 70/2013 አውጥቶ ሥራ ላይ ማዋሉ ይታወሳል፡፡
ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡
ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!