የሀገር ውስጥ ዜና

አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ የዓለም የምግብ እና እርሻ ድርጅት ዳይሬክተር ጋር ተወያዩ

By Mikias Ayele

September 14, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 4፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በጣልያን የኢትዮጵያ አምባሳደር ደሚቱ ሀምቢሳ የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት ዳይሬክተር ጄኔራል ቁ ዶንግዩ ጋር ተወያዩ፡፡

በውይይታቸውም አምባሳደር ደሚቱ ወቅታዊ የኢትዮጵያን ጉዳይ በተመለከተ መንግሥት በሰሜን ኢትዮጵያ ያለው ግጭት በአፍሪካ ሕብረት በኩል በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ያለውን ቁርጠኝነት አብራርተዋል፡፡

አክለውም የአሸባሪው ህወሓት ወረራ በአካባቢው የግብርና ዘርፍ ላይ ተፅኖ ማሳደሩን አስረድተዋል፡፡

የህወሓት አሸባሪ ቡድን የሰላም አማራጮችን በመተው የጥፋት ጦርነቱን መቀጠሉን በዚህም ንጹሃንን እያጠቃ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ንብረት እያወደመ መሆኑን እና ሰብዓዊ እርዳታዎችን ለጦርነት እየተጠቀመ ስለመሆኑም አስገንዝበዋል፡፡

ህጻናትን ለጦርነት በመመልመል አካባቢውን የማተራመስ ተግባሩን አጠናክሮ እንደቀጠለበት ለዋና ዳይሬክተሩ ማስረዳታቸውን ከኤምባሲው ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡