በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ተወያዩ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በመዲናዋ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳይ ላይ ከአስተዳደሩ ጋር ተወያይተዋል።
በየካ ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት የትግራይ ተወላጆች አሸባሪው ሕወሓት ለትግራይ ህዝብ የወገነ መስሎ በህዝቡ ላይ የሚያደርሰውን ጫና እና በደል ሊያቆም ይገባል ሲሉም ድርጊቱን ኮንነዋል።
የትግራይ ህዝብ ሠላም ወዳድ እና ከሌሎች ብሔር ብሔረሰብ ወድምና እህቶቹ ጋር ተስማምቶ የሚኖር ህዝብ ነው ብለዋል፡፡
በመሆኑም ዓላማ ለሌለው ጦርነት ህዝቡ እየተሰቃየ በመሆኑ መንግስት ሊደርስለት ይገባል ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል።
በልደታ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በበኩላቸው፥ አጥፊውን ከሠላማዊ ዜጎች መለየት እንደሚያስፈልግና በኢትዮጵያ ጉዳይ እንደማይደራደሩ በመጠቆም ከሌሎች ህዝቦች ጋር ሆነን ቡድኑን እንታገላለን ብለዋል፡፡
ከጦርነት የሚገኝ መፍትሄ የለም ሠላምን በመምረጥ ህዝብን ከችግር ማውጣት ይገባል ሲሉም ነዋሪዎቹ ተናግረዋል።
በቂርቆስ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆች በበኩላቸው የትግራይ ሕዝብ ከርሃብ ጋር እየታገለ መሆኑን ጠቁመው ÷ “እኛ ጦርነት አንፈልግም፤ ጦርነት ለማንም አይበጅም ብለዋል፡፡
በአቃቂ ቃሊቲ ክፍለ ከተማ የሚኖሩ የትግራይ ተወላጆችም ÷ እንደ ኢትዮጵያዊ ከወንድሞቻችን እና እህቶቻችን ጋር በመሆን ኢትዮጵያን ወደ ሠላም ማምጣት አለብን ብለዋል፡፡
ዜጎቿ በሠላም ወጥተው በሠላም የሚገቡባት ኀገር እንድትሆንም እንሰራለን ነው ያሉት፡፡
መንግስትም የኅግ ማስከበር ሥራ በሚሰራበት ወቅት የአሸባሪውን ተላላኪዎች እና አቀባዮች የሆኑትን መለየት እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡
በስመ የትግራይ ተወላጅ ሁሉም በአንድ ዐይን መታየት እንደሌለበትም ነው የተናገሩት፡፡
ለመጭው ትውልድ ለልጆቻችን ሠላም እንጂ ጦርነት አናወርስም፤ ከመንግስት ጎንም በመቆም የትግራይ ክልል ብሎም የሀገራችን ሠላም እንዲሰፍን አብሮነታችንን እናሳያለን ማለታቸውንም ከክፍለ-ከተሞቹ ኮሙኒኬሽን ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡