የህወሓት የሽብር ቡድን በሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ከፍተኛ ማህበራዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱ ተገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 5፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የህወሓት የሽብር ቡድን በወረራ ይዟቸው በነበሩ የሰሜን ጎንደር አካባቢዎች ከፍተኛ ማህበራዊ እና ሰብዓዊ ጉዳት ማድረሱን የሰሜን ጎንደር ዞን ገለጸ፡፡
የሰሜን ጎንደር ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ያለዓለም ፈንታሁን በሰጡት መግለጫ÷ የሽብር ቡድኑ በወረራ በያዛቸው አካባቢዎች አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ጨምሮ የመንግስት መስሪያ ቤቶችን፣ ሆስፒታሎችን፣ የትምህርት ተቋማትን፣ ሆቴሎችን እና መሰረተ ልማቶችን በመዝረፍና በማውደም ዳግም አገልግሎት እንዳይሰጡ ማድረግ ብለዋል።
ቡድኑ የማህበረሰቡን ስነ ልቦና የሚያቀጭጩ ተግባራትንም ፈፅሟል ነው ያሉት።
የደረሰው ሰብዓዊ ጉዳት ወደፊት በጥናት እንደሚገለጽ ጠቅሰው÷የሽብር ቡድኑ ሕፃናትን መድፈሩን፣ ወጣቶችን አፍኖ መውሰዱን፣ በርካቶችን መግደሉን እና የተለያየ በደል ሲፈጽም መቆየቱን በመግለጫቸው አንስተዋል።
የሽብር ቡድኑ የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመተው ዳግም ትንኮሳ እና ወረራ የጀመረ በመሆኑ ጥምር ጦሩ በተደራጀ መልኩ አስፈላጊውን ምላሽ እየሰጠው እንደሚገኝ ነው የገለጹት።
የዞኑ ማህበረሰብ ለጥምር ጦሩ ከደጀንነት ጀምሮ የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ይገኛልም ነው ያሉት የዞኑ አስተዳዳሪ።
በአሁን ሰዓት የአዲዓርቃይ ከተማ ነዋሪዎችን ጨምሮ በዙሪያው ያለው ማህበረሰብ አስቸኳይ ሰብዓዊ ድጋፍ እንደሚያስፈልገውም ገልጸዋል።
ህወሓት አሁንም ሰላም ፈላጊ በመምሰል ዓለም አቀፉን ማህበረሰብ በማደናገር እየሰራ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው÷ ከአማራ ሕዝብ ጠብ የለኝም በማለት በመሸንገል ላይ እንደሚገኝ እና ታሪክ ይቅር የማይለው ድርጊት በሕዝቡ ላይ መፈፀሙንም በመግለጫው ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያውያን እና የኢትዮጵያ ወዳጆች ሲያደርጉት የነበረውን ሁለንተናዊ ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉና ህብረተሰቡን እንዲያግዙ እንዲሁም ከጥምር ጦሩ ጎን እንዲቆሙ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በምንይችል አዘዘው