Fana: At a Speed of Life!

በመከላከያ ሰራዊት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በየደረጃው ግብረ ሃይል ተቋቁሟል

አዲስ አበባ ፣ መጋቢት 9፣ 2012 (ኤፍ ቢ ሲ) በሀገር መከላከያ ሰራዊት የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በየደረጃው ግብረ ሃይል መቋቋሙን የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ጄነራል አደም መሃመድ ገለጹ።

ጄነራል አደም የኮሮና ቫይረስ በሀገሪቱ መከሰቱን ተከትሎ በመከላከያ ሰራዊት ውስጥ ቫይረሱን መከላከል በሚቻልባቸው ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም የመከላከያ ሰራዊት በሃገር ውስጥ እና በተለያዩ ሀገራት በሰላም ማስከበር ግዳጆች ላይ ተሰማርቶ የሚገኝ መሆኑን አውስተዋል።

ሰራዊቱ ሃገርንና ህዝብን ከተፈጥሯዊና ሰው ሰራሽ ችግሮች ለመከላከል ብሎም የተጣለበትን ሃላፊነት በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት ጤንነቱን መጠበቅ እንዳለበት አንስተዋል።

በአሁኑ ወቅት በሀገሪቱ የተከሰተውን የኮሮና ቫይረስ ለመከላከልም በመከላከያ ሰራዊቱ ውስጥ በሁሉም ደረጃዎች ግብረ ሃይል መቋቋሙን ተናግረዋል።

አዲስ የሰራዊት አባል ምልመላ እና ፈቃድ እንደማይኖር የገለጹት ጄነራል አደም፥ የሰራዊቱ አባላት በሚኖሩባቸው ካምፕና መኖሪያ ቤቶች ለደህንነት ሲባል ከአባላት ጋር የሚኖራቸውን ንክኪ እንዲገቱም አሳስበዋል።

ከዚህ ጋር ተያይዞ የሰራዊት አባላቱ ቫይረሱን ለመከላከል የሚያስችሉ ቅድመ ጥንቃቄዎችን በተገቢው ሁኔታ መተግበር እንዳላባቸው ጥሪ አቅርበዋል።

የመከላከያ ሰራዊት አባላት ስለበሽታው ግንዛቤ እንዲያገኙና ራሳቸውን እንዲጠብቁ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስራ እየተሰራ ነው ማለታቸውን ከኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።

ትኩስ መረጃዎችን በፍጥነት ለማግኘት የቴሌግራም ገፃችንን ሰብስክራይብ ያድርጉ!
https://t.me/fanatelevision

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.