Fana: At a Speed of Life!

በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓትን ተጠያቂ ማድረግ አለበት- ፕ/ር አን ፊትዝ

 

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል ያለው ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ አሸባሪው ህወሓትን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ ገለጹ።

 

በካናዳ ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች ተመራማሪ እና የባልሲሊ ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ትምህርት ቤት ዲን ፕሮፌሰር አን ፊትዝጌራልድ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ባደረጉት ቆይታ÷ የኢትዮጵያ መንግስት በሰሜኑ የሀገሪቱ ክፍል የተፈጠረውን ግጭት በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በርካታ ጥረቶች ማድረጉን አንስተዋል፡፡

 

ለዚህም መንግስት በፈረንጆቹ ሰኔ ወር 2021 የተናጠል ተኩስ አቁም ማወጁን እና በተያዘው ዓመት መጋቢት ወር ላይ ወደ ትግራይ ክልል የሰብዓዊ እርዳታ እንዲገባ የሰብዓዊ ተኩስ አቁም ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡

 

ይሁን እንጂ አሻባሪው ህወሓት የቀረበለትን የሰላም ጥሪ በመግፋት ትንኮሳውን አጠናክሮ መቀጠሉን ነው ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ ያብራሩት፡፡

 

በአንድ ሀገር ውስጥ አማጺ ቡድኖች በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት በመክፈት የሀገርን ሉዓላዊነት የሚዳፈሩ ከሆነ ዜጎችን የመጠበቅ ሃላፊነት ያለበት መንግስት እጁን አጣጥፎ መቀመጥ እንደሌለበት መገንዘብ እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

 

ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሰሜኑ የኢትዮጵያ ክፍል የተፈጠረው ግጭት መፍትሄ እንዲያገኝ ለሰላማዊ ውይይት በሩን የዘጋውን አሸባሪው ህወሓትን ተጠያቂ ማድረግ እንዳለበትም አስረድተዋል፡፡

 

ከጉዳዩ ጋር ተያይዞ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ ማዕቀብ መጣሉን ያስታወሱት ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ÷ በአባሸሪው ህወሓት እና አመራሮቹ ላይ ግን ምንም አይነት ማዕቀብ አለመጣሉን አንስተዋል፡፡

 

ስለሆነም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የቀረበለትን ሰላማዊ ውይይት በተደጋጋሚ ውድቅ በሚያደርገው አሸባሪው ህወሓት ላይ ተመጣጠኝ ማዕቀብ መጣል እንዳለበት ነው አጽንኦት የሰጡት፡፡

 

አሸባሪው ህወሓት ሀገሪቱን ለ27 አመታት መምራቱን ያስታወሱት ፕሮፌሰሯ፥ ይህም በዓለም አቀፉ ዲፕሎማሲ ስራ ብልጫ እንዲወስድ በማድረጉ የአማፂው ቡድን ሀሳብ ብቻ እንዲሰማ መልካም አጋጣሚ ፈጥሮለታልም ነው ያሉት፡፡

 

የአሸባሪው ቡድን አመራሮች ለስልጣን ካላቸው ከፍተኛ ጥማት የተነሳ ግጭቱን ማስቆም እንደማይፈልጉ በማውሳትም፥ ጦርነቱን ማስቀጠል ለእነሱ የህልውና ጉዳይ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

 

ዓለም አቀፍ የጸጥታ ጉዳዮች ተመራማሪዋ ፕሮፌሰር አን ፊትዝ ጌራልድ ግጭቱን ለማስቆም ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በአፍሪካ ኅብረት የሚመራውን የሰላም ውይይት እንዲደግፍም ጠይቀዋል።

 

ጦርነቱ በማንኛውም መስፈርት አክሳሪ እና መቀጠል የሌለበት መሆኑንም አጽንኦት ሰጥተው ተናግረዋል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.