Fana: At a Speed of Life!

የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አመራርና ሰራተኞች ለመከላከያ ሠራዊት ደም ለገሱ

አዲስ አበባ ፣ መስከረም 6 ፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሕፈት ቤት አመራርና ሰራተኞች ለሀገር መከላከያ ሠራዊት ደም ለግሰዋል።

በፅሕፈት ቤቱ የብቃትና ሰው ሃብት አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሽብሩ አባዲማ በዚህ ወቅት እንደተናገሩት ሰራተኞችና አመራሮች ከዚህ ቀደም የተለያዩ ድጋፎችን በማድረግ ለሠራዊቱ ያላቸውን ደጀንነታቸውን በተግባር አረጋግጠዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም ለኢትዮጵያ ሉዓላዊነት መጠበቅ በጀግንነት እየመከተ ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የደም ልገሳ ማከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

የፅህፈት ቤቱ ሠራተኞች በበኩላቸው፥ ሠራዊቱ ውድ ህይወቱን ለእኛ ሲሰጠን እኛ ደግሞ ትንሿን ደማችንን ለመስጠት አንሰስትም ነው ያሉት።
መከላከያ ሰራዊቱ ሀገር ለማፈራረስ ከውስጥም ከውጭም የተነሱ ኃይሎችን ሴራ በመከላከል የሀገር ህልውናን እያስጠበቀ መሆኑን ጠቅሰው፥ እኛ ለእነዚህ የሀገር አለኝታዎች ደም በመለገሳችን እድለኞች ነን ብለዋል።

በዱር በገደሉ እየተፋለመ የሚገኘው ሠራዊት ለሃገር ህልውና የሚያደርገውን ተጋድሎ ለማሳካት ከደም ልገሳ ባሻገር ለመደገፍ ዝግጁ ነን ማለታቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ ዘርፈ ብዙ ፈተናዎች እንደተደቀኑባት ያነሱት ሠራተኞቹና አመራሮቹ ጊዜያዊ ፈተናዎችን ለመሻገር ኢትዮጵያውያን አንድነታቸውን ማጠናከር እንደሚገባቸው ገልጸዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ፅሐፈት ቤትና በስሩ የሚገኙ ተቋማት ሠራተኞቻቸውን በማስተባበር ለሰራዊቱ ከ90 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት የዓይነትና የገንዘብ ድጋፍ ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.