Fana: At a Speed of Life!

ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ ተደረገ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 8፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ለሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ለኢፌዴሪ አየር ኃይል ከ12 ሚሊየን ብር በላይ ግምት ያለው የአይነት ድጋፍ ተደረገ፡፡

 

የሰሜን ሸዋ ዞን አስተዳደር በስሩ ካሉ ወረዳና ከተሞች ያሰባሰበውን ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ደረቅ ሬሽን ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፍ አድርጓል።

 

የዞኑ አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ተማለደ በላይሁን ወልደያ ከተማ በመገኘት ራያ ግንባር ለሚገኘው የሀገር መከላከያ ሰራዊት ድጋፉን አስረክበዋል።

 

አሸባሪው የህወሓት ቡድን ለሶስተኛ ጊዜ ጦርነት በመክፈት የህዝባችንን ስቃይ በማብዛት ክፋቱንና ባንዳነቱን አሳይቷል ያሉት ሃላፊው ይህንን የህወሓት እኩይ ተግባር ለመመከት በሚደረገው ጥረት የዞኑ ህዝብ የደጀንነት ስራውን አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል፡፡

 

ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ ዞን አስተዳደር ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ፋሲል አረጋ ÷ድጋፉ አስፈላጊ በሆነበት ሰዓት የደረሰ መሆኑን ገልፀው በቀጣይም ሌሎች አካላት ድጋፋቸውን አጠናክረው እንድቀጥሉ ጥሪ አስተላልፈዋል።

 

በሌላ በኩል የቦሌ ክፍለ ከተማ ከአዲስ አበባ ከንቲባ ፅ/ቤት ጋር በመተባበር ለኢፌዴሪ አየር ኃይል ከ6 ሚሊየን ብር በላይ የሚገመት ሰንጋዎች፣ በጎች፣ እሽግ ጁስ፣ እና ሌሎች የምግብ እቃዎች እንዲሁም ለሕክምና አገልግሎት የሚውሉ የተለያዩ መድኃኒቶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡

 

የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ዋና ሥራ አስፈጻሚ ወይዘሮ ዓለምጸሐይ ሺፈራው ድጋፉን ባስረከቡበት ወቅት ባደረጉት ንግግር÷ያደረግነው ድጋፍ ሠራዊታችን ከሚከፍለው መስዋዕትነት አንፃር ትንሽ ነው ያሉ ሲሆን የክፍለ ከተማው አስተዳደር ኅብረተሰቡን በማስተባበር ለሠራዊቱ ያለውን አጋርነት አጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

 

ድጋፉን የተረከቡት የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተና ጄኔራል ይልማ መርዳሳ ÷ ድጋፉ አየር ኃይሉ የሕዝቡን ደጀንነት ይዞ በተሻለ ቁመና ላይ እንዲገኝ የሞራል ጉልበት እንደሚሆነው በመግልጽ የቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

 

በለይኩን አለም ተጨማሪ መረጃ የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ፅህፈት ቤት
You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.