Fana: At a Speed of Life!

ቻይና ከማርስ ያገኘቻቸውን ሳይንሳዊ የምርምር ውጤቶች ይፋ አደረገች

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) ቻይና በማርስ የጠፈር ምርምሯ ያገኘቻቸውን ውጤቶች ይፋ አደረገች፡፡

የቻይና ብሄራዊ የጠፈር አስተዳደር ይፋ ባደረገው ውጤት መሰረት የቻይና ተመራማሪዎች በማርስ አቀማመጥና አጠቃላይ ገጽታ አፈጣጠር እና በውሃ እንቅስቃሴዎች መካከል ያለውን ግንኙነት በተመለከተ ገለፃ አድርገዋል፡፡

ተመራማሪዎቹ በቀይዋ ፕላኔት ከ1 ቢሊየን አመታት በፊት ጀምሮ የፈሳሽ ውሃ እንቅስቃሴ መኖሩን የሚያመላክቱ እርጥበት አዘል ማዕድኖች ማግኘታቸውን አስታውቀዋል፡፡

ባረፉበት የማርስ ክፍል የፕላኔቷ አፈር በውሃ እና በነፋስ መሸርሸር ሳያጋጥመው እንዳልቀረ የሚያመላክቱ ማስረጃዎችን አግኝተናልም ነው ያሉት።

በማርስ ላይ የሚገኘው አፈር ከፍተኛ እርጥበት የመሸከም አቅም እና ዝቅተኛ የእፍግታ መጠን እንዳለው አመላካች ውጤት ማግኘታቸውንም ገልጸዋል።

ከግኝታቸው በመነሳትም በፕላኔቷ ላይ ያለው የንፋስና የውሃ እንቅስቃሴ በማርስ ገጽታ ዝግመተ ለውጥ እና አካባቢ ላይ የሚያሳድሩት ተፅዕኖ፥ በፕላኔቷ ላይ በሚገኘው ዩቶፒያን ፕላኒሺያ በተባለ ስፍራ ውቅያኖስ ነበር ለሚለው መላምት አጋዥ መሆኑንም ጠቅሰዋል።

በተጨማሪም በማርስ ላይ ስላለው የድንጋይ ጥግግት እና የመሬት መሸርሸር መጠን እንዲሁም የማርስ የስበት መጠንን በተመለከተ በርካታ ሳይንሳዊ ውጤቶችን አግኝተናል ብለዋል።

የቻይና ብሄራዊ የጠፈር አስተዳደር ለወደፊት ፕላኔቷን በተመለከተ የርቀት ዳሰሳ ጥናቶችን እና ሳይንሳዊ መረጃዎችን መሰበሰቡን እንደሚቀጥል ማስታወቁን ሲ ጂ ቲ ኤን ነው የዘገበው፡፡

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.