Fana: At a Speed of Life!

ፋና በሚዲያው ዘርፍ የሰለጠነውን አለም ተሞክሮ በመቀመር ለሀገሪቱ ልማትና መልካም ገፅታ እንደሚሰራ ዋና ስራ አስፈጻሚው አስታወቁ

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በሚዲያው ዘርፍ የሰለጠነውን አለም ተሞክሮ ወደ አገር ቤት በማምጣት ለአገራችን የመልካም ገፅታ ግንባታ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፓሬት ዋና ስራ አስፈጻሚ አስታወቁ።

የተቋሙ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ አድማሱ ዳምጠው ይህን የተናገሩት በኳታር የአልጀዚራ ስቱዲዮን በጎበኙበት ወቅት ነው።

የሚዲያ ተቋሙ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን በመታጠቅና በአግባቡ በመጠቀም ቀዳሚ የመረጃ ምንጭ ለመሆንና ለአገራችን ሁለንተናዊ እድገት ጠቃሚ የሆኑ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ለማድረስ ትኩረት ሰጥቶ ይሰራል ብለዋል አቶ አድማሱ ።

የአለም አቀፍ ሚዲያዎችን ልምድ መቀመር የአገርንና የህዝብን ጥቅም ባስቀደመ መልኩ የሚሰሩ መረጃን ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ትልቅ ጠቀሜታ እንዳለዉም ጠቅሰዋል።

ከዚህ አኳያ ፋና ከአገር ውስጥ አልፎ በአለም መድረኮች ሁሉ የኢትዮጵያን መልካም ገፅታ ሊገነቡ ለሚችሉ መረጃዎች ትኩረት በመስጠት እንደሚሰራም ተናግረዋል ዋና ስራ አስፈጻሚው።

በአልጀዚራ ስቱዲዮ በተደረገው ጉብኝትም የሚዲያ ስራ በሙያ ብስለትና የሀገርንና የህዝብን አደራ ማዕከል መልኩ ሊከናወን እንደሚገባ ተገንዝበናል ነው ያሉት።

ስራን ለማቀላጠፍም አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀም አስፈላጊ መሆኑን ከጉብኙቱ የበለጠ መገንዘባቸውን ነው የገለፁት።

ፋና ከዚህ አኳያ ምርጥ የአለም ሚዲያ ልምዶችን በመቀመር ለአገር ልማትና እድገት የበኩሉን ሚና ለመወጣት በላቀ ተነሳሸነት እንደሚሰራ ጠቅሰዋል።

የአልጀዚራ ሚዲያ ኔትዎርክ ስልጠና ማዕከል ዋና ዳይሬክተር ዶክተር ኢማን አል አምሪ በበኩላቸው፥ አልጀዚራ በሚዲያው ዘርፍ ልምድ ለማካፈል በሙያተኛ ስልጠናና ቁሳቁስ ድጋፍ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋር ለመስራት ዝግጁ መሆኑን አረጋግጠዋል።

ዘርፉ የሚጠይቀውን ዘመናዊ ቴክኖሎጂ መታጠቅ አስፈላጊ መሆኑን የገለፁት ዋና ዳይሬክተሯ፥ ሚዲያን በዕውቀት መስራት እና መምራት ያሻልም ብለዋል፡፡

በዚህም አልጀዚራ የተቋቋመለትን ዓላማ ከግብ ማድረስ መቻሉን ገልፀው፥ ፋናም በዚህ ረገድ ልምድ ያለው ሚዲያ ስለመሆኑ ከዚህ ቀደም የሚዲያ ተቋሙን ከጎበኙ ባልደረቦቼ ተረድቻለሁ ብለዋል፡፡

የአልጀዚራ ሚዲያ ኢንስቲትዩት ሀላፊ ሙንተሰር ማራይ በበኩላቸው ፋና ተወዳጅ መሆኑን ተናግረው፥ አለምአቀፍ ተፅዕኖ ፈጣሪ፣ ተወዳዳሪ፣ በየሚዲያው አማራጭ ሁሉ የላቀ ተደራሽ፣ ባለብቁ ሙያተኞች እንዲሆን እና የተሻለ ጥራት ያላቸው ይዘቶችን እንዲሰራ ተቋማቸው ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደሚያደርግ እና በቅርበት ከፋና ጋር መስራት እንደሚፈልግ ገልፀዋል፡፡

በተለይ ዘርፉ ተለዋዋጭ በመሆኑ ወቅቱ የሚጠይቀውን ዕውቀትና ክህሎት ተላብሶ መምራት ተወዳዳሪ ያደርገዋል፤ በዚህ ረገድ የአልጀዚራ ሚዲያ ኢንስቲትዩት የካበተ ልምድ ባላቸው ባለሙያዎቹ አማካኝነት ድጋፍ ያደርጋልም ብለዋል፡፡

ወቅታዊ፣ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ድረ ገጽ፦ https://www.fanabc.com/
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/fanabroadcasting
ዩትዩብ፦ https://www.youtube.com/c/fanabroadcastingcorporate/
ቴሌግራም፦ https://t.me/fanatelevision
ትዊተር፦ https://twitter.com/fanatelevision በመወዳጀት ይከታተሉን፡፡

ዘወትር፦ ከእኛ ጋር ስላሉ እናመሰግናለን!

You might also like

Leave A Reply

Your email address will not be published.