በ130 ሚሊየን ዶላር የተገነባው “የሬድ ፎክስ” የመረጃ ማዕከል አገልግሎት መስጠት ጀመረ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ ፓርክ በ130 ሚሊየን ዶላር የተገነባው “የሬድ ፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ” የመረጃ ማዕከልና ዋና መስሪያ ቤት በይፋ አገልግሎት መስጠት ጀምሯል፡፡
የአገልግሎት ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ የኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሳንዶካን ደበበን ጨምሮ የሬድፎክስ ሶሉሽንስ ግሩፕ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ አዳነ ካሳዬ እንዲሁም ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች፣ ሰራተኞች እና ሌሎች እንግዶች በተገኙበት ተከናውኗል፡፡
በዚሁ ወቅት አቶ ሳንዶካን ደበበ ኩባንያው በአጭር ጊዜ ኢንቨስትመንቱን እውን ማድረጉ በዘርፉ በቂ እውቀት፣ ልምድ እና ፅናት ያለው ስለመሆኑ የሚያረጋግጥ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
ለኢትዮጵያ በዘርፉ ኢንቨስትመንትን ብቻ ሳይሆን ዘላቂ መፍትሄ ይዞ የመጣ ስለመሆኑ ማሳያ መሆኑንም ገልፀዋል።
ትኩረት ከተሰጠባቸው የኢንቨስትመንት ዘርፎች ውስጥ ኢንፎርሜሽን ኮሙኒኬሽን ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቅሰው፥ መሰል ኢንቨስትመንቶችን ለመሳብ እና ለመደገፍ የሚደረገው እንቅስቃሴ መቀጠሉንም አንስተዋል።
“ሬድፎክስ” አላማው በተሟላ የመረጃ ማዕከል ግንባታ በዘርፉ የኢትዮጵያን አቅም ማሳደግ እንደሆነ መገለጹን ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን የተገኘው መረጃ ያመላክታል፡፡