የሀገር ውስጥ ዜና

የመስቀል፣ ደመራና ኢሬቻ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ሊጠናከሩ ይገባል ተባለ

By ዮሐንስ ደርበው

September 19, 2022

አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በዩኔስኮ የተመዘገቡት የመስቀል፣ ደመራና ኢሬቻ በዓላት አከባበር ደማቅና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ እንዲጠናቀቅ በመሠረተ ልማትና አገልግሎት ሰጪ ተቋማት እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት በተቀናጀ አግባብ ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተገለፀ።

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ ዋና ስራ አስኪያጅ ጥራቱ በየነ በመስከረም ወር በአዲስ አበባ ከተማ የሚከበሩት ሁለቱ በዓላት ባህላዊና ሐይማኖታዊ እሴትና ትውፊታቸው ተጠብቆ እንዲከበሩ እስካሁን በሚመለከታቸው ተቋማት እየተደረገ ያለውን የቅድመ ዝግጅት ሥራ ገምግመዋል።

በውይይቱ ላይ ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይልና ከአዲስ አበባ ቅርንጫፍ የኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት፣ ከመንገዶች ባለስልጣን፣ ከእሳት አደጋ፣ ከከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ፣ ከዲዛይንና ግንባታ ሥራዎች ቢሮ፣ ከትራንስፖርት ቢሮ፣ ከፅዳት፣ ቄራዎችና ሌሎች ተቋማት አመራሮች በየተቋማቸው የተከናወኑ የቅድመ ዝግጅት ተግባራት ያሉበትን ደረጃ ሪፖርት አቅርበዋል።

አቶ ጥራቱ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት÷ በዓላቱ ያለ ምንም የፀጥታ ስጋት እንዲከበሩ በአዲስ ዓመት አከባበር ወቅት የተከናወኑ ተግባራትን በመልካም ተሞክሮነት መውሰድ ይገባል ብለዋል።

በቅርቡ ለሚከበሩት እነዚህ ሕዝባዊና የዐደባባይ በዓላት የመብራት፣ የውኃ፣ የፅዳት፣ የእሳት አደጋ መከላከልና ሌሎች ለበዓሉ አከባበር ወሳኝ የሆኑ አገልግሎቶች በቅንጅት በአፋጣኝ እንዲፈጸሙ አሳስበዋል።

ይህን ቅንጅታዊ ሥራም የከተማዋን ነዋሪዎች በማሳተፍና በማስተባበር እስከ በዓላቱ ፍፃሜ ድረስ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አመላክተዋል፡፡

የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችም ሥራውን በቅርብ ድጋፍና ክትትል መምራቱን ይቀጥላል ማለታቸው የከንቲባ ጽሕፈት ቤት መረጃ ያመላክታል፡፡