አንዳንድ ሀገራትና ተቋማት አሸባሪው ህወሓት የፈጸማቸውን አሰቃቂ ወንጀሎች ደብቀዋል – ምሁራን
አዲስ አበባ፣ መስከረም 9፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) አሸባሪው የህወሓት ቡድን የተለያዩ ወንጀሎችንና በደሎችን ቢፈጽምም አንዳንድ ሀገራትና ተቋማት የሚከተሉት የተዛባ አካሄድ እውነታው እንዳይወጣ አድርጓል ሲሉ ምሁራን ተናገሩ፡፡
በወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ጉዳዮች ተመራማሪው ንጋቱ አበበ ከፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬትጋር በነበራቸው ቆይታ÷ በአንዳንድ ሀገራት እና በሽብር ቡድኑ መካከል ያለው የላኪና የተላላኪ ግንኙነት ከእውነታ በተቃርኖ እንዲቆሙ አድርጓል ብለዋል፡፡
ቡድኑ ከማይካድራ እስከ ጭና፣ ከጋሊኮማ እስከ አጋምሳ በርካታ ግፎች መፈፀሙን አንስተው÷ ይሁን እንጂ እነዚህን የሽብር ቡድኑ ግፎች ተቋማትና ሀገራት በሚገባቸው ልክ እንዳላነሷቸው ጠቁመዋል፡፡
በጎንደር ዩኒቨርሲቲ የህግ መምህሩ እና የሽብር ቡድኑ የፈፀማቸውን ወንጀሎች ያጠናው የጥናት ቡድን አባል የሆኑት አቶ ልጃለም ጋሻው በበኩላቸው÷ አሸባሪው ህወሐት ከፍጥረቱ ጀምሮ በርካታ አሰቃቂ ወንጀሎችን ሲፈጽም መቆየቱን አንስተዋል
ምሁራኑ የሽብር ቡድኑ አያሌ ጥፋቶችን እና ሰብዓዊ ችግሮችን ቢፈጥርም አንዳንድ ሀገራትና ተቋማት ከቡድኑ ጎን በመቆም እውነታውን ሲያዛቡ እንደተስተዋሉ አብራርተዋል፡፡
ችግሩን ለመፍታት መንግስት ተደጋጋሚ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች ማድረግ እንደሚገባው የጠቆሙት ምሁራኑ÷ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል የህወሓትን ወንጀሎች በመረጃ ለማጋለጥ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጠይቀዋል፡፡
በአፈወርቅ እያዩ