“ዩኔስኮ“ ኢትዮጵያ የምታዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እንደሚደግፍ ገለጸ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 10፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) ኢትዮጵያ የምታዘጋጀውን ዓለም አቀፍ የበይነ መረብ አስተዳደርን ጨምሮ የተለያዩ ስራዎችን እንደሚደግፍ ገልጿል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ ከዩኔስኮ የኢትዮጵያ ተወካይ ዳይሬክተር ዶክተር ሪታ ቢሶኑዝ ጋር በተለያዩ መስኮች በጋራ መስራት በሚያችሉ ጉዳዮች ላይ ተወያይተዋል።
በውይይታቸውም በዓለም አቀፉ የበይነ መረብ አስተዳደር ጉባኤ፣ በመንግስት የኤሌትሮኒክስ አገልግሎት፣ በዲጂታል ክህሎት፣ በሳይንስ፣ በኢንጂነሪንግ እና ሂሳብ ዘርፎች ላይ መክረዋል፡፡
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላበዚሁ ወቅት የኢትዮጵያ ቅርብ አጋር የሆነው “ዩኔስኮ” በሳይንስ ቴክኖሎጂ እና ኢኖቬሽን ዘርፍ የኢትዮጵያን ጥረት ለመደገፍ ለሳየው ፍላጎት አመስግነዋል።
የዲጂታል ኢትዮጵያ 2025 ስትራቴጂን ተቀርጾ ለተግባራዊነቱ እየተሰራ መሆኑን ጠቅሰው÷”ከዩኔስኮ“ ጋር በዘርፉ በጋራ ለመስራት የሚያስችሉ የትብብር ማዕቀፎችን በማዘጋጀት ወደ ስራ እንገባለንም ነው ያሉት፡፡
ዶክተር ሪታ ቢሶኑዝ በበኩላቸው “የዩኔስኮ“ ኢትዮጵያ በዚህ አመት የምታስተናግደውን ዓለም አቀፉን የበይነ መረብ አስተዳዳር ጉባኤ ለመደገፍ ፍላጎት እንዳለው ገልፀዋል።
በዲጂታል ክህሎት፣ በሰው ሰራሽ አስተውሎ፣ በመንግስት የኤሌክትሮኒክስ አገልግሎት እና በሌሎች ዘርፎች ላይም አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርጉ መናገራቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያመላክታል።