ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፍሪካን ወደ ሌላ “ቀዝቃዛ ጦርነት” ውስጥ እንዳይከታት ተጠየቀ
አዲስ አበባ፣ መስከረም 11፣ 2015 (ኤፍ ቢ ሲ) የሴኔጋል ፕሬዚዳንት እና የአፍሪካ ኅብረት ሊቀ-መንበር ማኪ ሳል ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አፍሪካን ወደ ሌላ “ቀዝቃዛ ጦርነት” ውስጥ እንዳይከታት ጠየቁ፡፡
ማኪ ሳል ይህን ያሉት በኒውዮርክ በተካሄደው 77ኛው የተመድ ጠቅላላ ጉባዔ ላይ ነው፡፡
ሊቀመንበሩ በአሁኑ ጊዜ አፍሪካ “ከቀዝቃዛ ጦርነት” እሠጥ-አገባ ይልቅ ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ጋር የጋራ ተጠቃሚነቷን በሚያረጋግጡ አጋርነቶች ላይ መሥራት ትፈልጋለች ብለዋል፡፡
አፍሪካ ባለፈ የታሪክ ሸክም እጅግ እንደተሰቃየች እና አሁን ላይ የ“ቀዝቃዛ ጦርነት” ምንጭ መሆን እንደማትሻም አመላክተዋል።
ይልቁንም አፍሪካ የተረጋጋች እና ለአጋሮቿ ምቹ የሥራ ዕድል ያመቻቸች አኅጉር ሆና መቀጠል እንደምትሻም ጠቁመዋል፡፡
ማኪ ሳል ዓለም በሙቀት መጨመር ፣ በአሳሳቢ የደኅንነት ጉዳዮች፣ በጤና አደጋዎች እንዲሁም በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት ውጥረት ውስጥ እንደምትገኝ እና ማንም ነገ ምን እንደሚፈጠር እርግጠኛ በማይሆንበት ደረጃ ላይ እንደምትገኝ አስታውሰዋል፡፡
የተመድ የጸጥታው ምክር ቤት የተቋቋመበት መተዳደሪያ አንድ ዓላማ ሽብርተኝነትን መዋጋት እንደመሆኑ በጉዳዩ ላይ ከአፍሪካ ጋር ተቀራርቦ እንዲሰራ መጠየቃቸውን ሲ ጂ ቲ ኤን ዘግቧል፡፡