በከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚከታተል ግብረ ሃይል ተቋቋመ
አዲስ አበባ፣ መጋቢት 9፣ 2012(ኤፍ.ቢ.ሲ) በሁሉም ከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተገናኙ ጉዳዮችን የሚከታተል ግብረ ሃይል በሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ተቋቁሞ እየሰራ እንደሚገኝ ተገለጸ።
ግብረ ሃይሉ ከመጋቢት 7 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የከፍተኛ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ተማሪዎች የክፍል ውስጥ ትምህርት አቁመው አጋዥ መፅሐፍት (ሃንድ አውት)፣ ማጣቃሻ መፅሐፍት፣ በበይነ መረብ በመታገዝ እና ሶፍት ኮፒ ለቀጣዮቹ 2 ሳምንታት በግላቸው እንዲያነቡ አቅርቧል።
በዩኒቨርሲቲዎች ተማሪዎች እጃቸውን አዘውትረው እንዲያፀዱም የውሃ አቅርቦትን የማሻሻል፣ የመታጠቢያ ሳሙናዎችንና አስፈላጊ ግብዓቶችን የማሟላትና የማቅረብ ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም ሚኒስቴሩ ገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ስለቫይረሱ ለተማሪዎች እና ለከፍተኛ ትምህርት ተቋማት ማህበረሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ዩኒቨርሲቲዎች የተለያዩ መንገዶችን እየተከተሉ መሆኑ ተጠቁሟል።
በሁለት ሳምንታ እድሜያቸው ከ60 ዓመት በላይ የሆኑና የልብ ወይም የካንሰር እንዲሁም የስኳርና ሌሎች ተዛማጅ ህመሞች ያሉባቸው፣ የአስምና የመተንፈሻ አካላት ችግር ያሉባቸው ሠራተኞች ከሌሎች የበለጠ ጥንቃቄ ማድረግ እንደሚገባቸው መመከሩን ከሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።